ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድል የማስፋት ጥረቱ መቀጠል እንዳለበት ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድል ለማስፋት የሚደረገው ጥረት በግሉ ዘርፍም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተመላከተ፡፡
ዛሬ በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ማዕከል ያዘጋጀው 2ኛው የአፍሪካ ንግድና ኢንቨስትመንት ጉባዔ ላይ ÷ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ተወካዮች፣ የቢዝነስ መሪዎች፣ ሥራ ፈጣሪዎች፣ የኩባንያ ኃላፊዎችና ሌሎችም ተሳትፈዋል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በጉባዔው ላይ እንደገለጹት÷ የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ማዕከል ያዘጋጀው አኅጉራዊ የንግድና ኢንቨስትመንት ስብሰባ በቢዝነስ ተቋማት መካከል ትውውቅና ትብብርን የሚፈጥር ነው፡፡
ኢትዮጵያም በማዕድን፣ ቱሪዝም፣ ግብርና፣ አይ ሲ ቲ እና በመሰል ዘርፎች መሰማራት ለሚፈልጉ አልሚዎች የተመቼ ጸጋ ያላት ሀገር መሆኗንም አስታውቀዋል፡፡
በመሆኑም በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድል ለማስፋት የሚደረገው ጥረት በግሉ ዘርፍም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ማዕከል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አብዲናስር ተርኪ ÷ አፍሪካ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ለልማት ምቹ የሆኑ ዕድሎች ያሏት አኅጉር መሆኗን ገልጸዋል፡፡
አፍሪካ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባለቤት መሆኗ እንዲሁም የተለያዩ የተፈጥሮ ሃብቶች ስላሏትና በዕድገት ጎዳና ላይ በመሆኗ የበለጸገች አኅጉርን ለመገንባት ዕድሎችና ምቹ ሁኔታዎች ናቸው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የዛምቢያ ኢምባሲ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተቀዳሚ ጸሐፊ ማጆሪ ሜይላ በቱሪዝም፣ በማዕድንና መሰል የተፈጥሮ ሀብቶች ዛምቢያ የበለጸገች መሆኗን ገልጸው÷ እንደ ኢትዮጵያ ካሉ ሀገራት ጋር በትብበር ለመሥራት ዕድል አግኝተናል ሲሉ የጉባዔውን በጎ አጋጣሚ ጠቅሰዋል፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!