የሳዑዲ ዓረቢያ ኤምባሲ በሐረር የሚገኙ ቅርሶችን ለመንከባከብ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረር ከተማ የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶችን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ድጋፍ እንደሚያደርግ በኢትዮጵያ የሳዑዲ ዓረቢያ ኤምባሲ አስታወቀ፡፡
የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በኢትዮጵያ ከሳዑዲ ዓረቢያ አምባሳደር ፋሃድ አባይዳላህ አል ሁማየዳኒ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም በኢትዮጵያ እና በሳዑዲ ዓረቢያ መካከል ያለው ግንኙነት ታሪካዊ መሆኑን አቶ ኦርዲን አንስተዋል፡፡
የጁገል እና ሸዋል ኢድ በዓል ዓለም አቀፍ ቅርሶች መገኛ የሆነችውን ሐረር ለመጎብኘት አምባሳደሩ ያሳዩትን ተነሳሽነት አቶ ኦርዲን ማድነቃቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡
ባህልን በማስተዋወቅ፣ ታሪካዊ ቅርሶችንና ሙዝየሞችን በመጠበቅ እንዲሁም በመንከባከብ ረገድ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
አምባሳደር ፋሃድ አባይዳላህ አልሁማየዳኒ (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ በሐረር ከተማ የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶችን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ኤምባሲው ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡