የአፍሪካ ኀብረት የመሪዎች ጉባኤና የአስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሰባ የቅድመ ዝግጅት ስራ ላይ ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመጭው የካቲት ወር በአዲስ አበባ የሚካሄዱት 37ኛው የአፍሪካ ኀብረት የመሪዎች ጉባዔና 44ኛዉ የአስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሰባን አስመልክቶ እየተደረጉ በሚገኙ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ላይ ብሔራዊ ኮሚቴው ሁለተኛ ዙር ውይይት አካሄደ ።
ዛሬ በተካሄደው ውይይት በመጀመሪያው ዙር ስብሰባ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት የዝግጅቱ ኮሚቴ አባል የሆኑ ተቋማት በአንድ ወር ውስጥ ያከናወናቸውን ተግባራት ሪፖርት አቅርበዋል።
የብሄራዊ ኮሚቴው ሰብሰቢ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ÷ አመታዊ ስብሰባውን በተሻለ ስኬት ለማካሄድ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በቅርበት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በሪፖርቱም የጤና፣ የፀጥታ፣ ከተማዋን የማስዋብ፣ የሆቴል፣ የእንግዳ አቀባበል፣ የትራንስፖርት፣ የመስተንግዶ፣ የሚዲያ ሽፋን እና መሰረታዊ አገልግሎቶች የማሳለጥ ስራዎች ላይ የተከናወኑ ዝግጅቶች ቀርበዋል ።
እስካሁን ለተከናወኑ ተግባራት ተቋማቱን አድንቀው በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራት ላይ አምባሳደር ብርቱካን አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የዘንድሮው ጉባዔ እንደ መንግስት በልዩ ድምቀት እንዲዘጋጅ የታቀደ መሆኑን ገልጸው የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት የሚመጥን የተቋማት ቅንጅትና የስራ ትኩረት መኖር እንዳለበት በአፅንኦት ገልጸዋል ።