የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል ለተባባሪ አካላት ሲሰጥ የነበረውን ስልጠና አጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል ለተባባሪ አካላት ሲሰጥ የነበረውን ስልጠና አጠናቋል፡፡
ኮሚሽኑ በክልሉ በሚገኙ 8 ዞኖች እና 6 የከተማ አስተዳደሮች ከተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ተቋማት ለተለዩ ተባባሪ አካላት ነው በአዳማ ከተማ ስልጠናውን ሲሰጥ የነበረው፡፡
ተባባሪ አካላቱ ከኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ፣ ከመምህራን ማህበር፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪክ ማህበራት፣ ከእድሮች፣ ከአባገዳዎችና ከሀደ ስንቄዎች፣ ከፍርድ ቤት እንዲሁም ከወረዳዎች የተወከሉ ናቸው ተብሏል፡፡
በሥልጠናው ከምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፣ ከምስራቅ እና ምዕራብ አርሲ፣ ከምዕራብ፣ ከደቡብ፣ ከሰሜን እና ከምስራቅ ሸዋ ዞኖች እንዲሁም ከሸገር፣ ከአዳማ፣ ከቢሾፍቱ፣ ከአምቦ እና ከሻሸመኔ ከተማ አስተዳሮች የተውጣጡ ተባባሪ አካላትም እንደተሳተፉ ተጠቅሷል፡፡
በሥልጠናው ስለ ምክክሩ ምንነትና ፋይዳ፣ በኮሚሽኑ ስለሚከናወኑ ተግባራት እንዲሁም ተባባሪ አካላት በምክክሩ ሂደት የአጀንዳ ሀሳቦችን በመስጠት የሚካፈሉ ተሳታፊዎችን ስለሚለዩበት የአሰራር ሥነ ዘዴ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መደረጉ ተጠቁሟል፡፡
እንዲሁም ተባባሪ አካላቱ በየወረዳዎቻቸው ተመልሰው ተሳታፊዎችን በሚለዩበት ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችንም በውይይት እንዲለዩ በማድረግ የመፍትሄ ሀሳቦች ቀርበው መግባባት ላይ ተደርሶባቸዋል ነው የተባለው፡፡
በክልሉ ከሚገኙ 171 ወረዳዎች ከ14 ሺህ በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ ተሳታፊዎች እንደሚለዩ የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተሳታፊዎቹ በክልል ደረጃ ለሚካሄደው የአጀንዳ ሀሳቦች የማሰባሰቢያ መድረክ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችንም የሚወክሉባቸው መድረኮችን እንደሚያዘጋጁ ተገልጿል፡፡