Fana: At a Speed of Life!

ኮርፖሬሽኑ በምዕራብ ኦሞ ዞን በ5 ሺህ ሄክታር ላይ ሰብል ሊያለማ ነው

 

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምዕራብ ኦሞ ዞን በ5 ሺህ ሄ/ር መሬት ላይ የምርጥ ዘርና ወደ ውጭ ሀገራት የሚላክ ሠብል ማምረት ሊጀምር እንደሆነ ተገለጸ።

ኮርፖሬሽኑ የሰብል ልማቱን ለመጀመር በዞኑ ልዩ ስሙ ኮካ በተባለ አካባቢ የሚገኝ የእርሻ ቦታ ከክልሉ መንግስት የተረከበ ሲሆን፤ ስራ ለመጀመርም ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል።

በውይይቱ የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ክፍሌ ወ/ማርያም እንዳሉት÷ ኮርፖሬሽኑ ተልዕኮው ለመወጣት በመላ ሀገሪቱ ሰፋፊ ስራዎችን ጀምሯል።

ምርትና አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ባስቀመጠው የ5 ዓመት ስትራቴጂክ ማዕቀፍ የተለያዩ ዘሮችን፣ ለኢንዱስትሪ ግብአት ሊሆኑ የሚችሉ ሰብሎችን በተለያዩ አካባቢዎች ለማምረት ከያዘው ዕቅድ ውስጥ አንዱ በምዕራብ ኦሞ ዞን የሚጀምረው ስራ ነው ብለዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብሄረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ መቱ አኩ÷ ሠፊ የመልማት አቅም ባለው ምዕራብ ኦሞ ዞን አርብቶ እና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች መልካም ጅምር ታይቷል ብለዋል።

መሠል የልማት ስራዎች የአርብቶ አደሩን በዘላቂነት ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውን ገልጸው፤ ለስራዉ ለውጤታማነት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በዘላለም ግድየለው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.