ስለ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት
የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች እየተተገበረ የሚገኝ ሲሆን፥ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅና የሀገርን መዋዕለ ነዋይ በማሳደግ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ይነገራል፡፡
ፕሮጀክቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከዓመታት በፊት ያስጀመሩት ሲሆን፥ የጎርጎራ፣ ወንጪ እና ኮይሻ መዳረሻዎች በሚል ይጠቀሳሉ፡፡
የኮይሻ ፕሮጀክት የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክን፣ የግቤ 3 እና ኮይሻ ግድቦችና የአካባቢው ተፈጥሯዊ መስህቦችን የሚያስተሳስር በመሆኑ ፋይዳው ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል፡፡
የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነውና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በኮንታ ዞንና በዳውሮ ዞን መካከል የሚገኘው የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክም ከሰሞኑ እንደሚመረገቅ ተገልጿል፡፡
በዚህም ፕሮጀክቱ የሀገር ገቢን ከማሳደግ ባለፈ ለአካባቢው ህዝብ በተለየ ሁኔታ ደግሞ የቱሪዝም ፍሰትን በመጨመር እንዲሁም የስራ እድል በመፍጠር ረገድ ሚናው ከፍተኛ መሆኑም ነው የሚገለጸው፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ የሦስቱ መዳረሻዎችን ለማልማት ኢትዮጵያውያን በተለያየ ጊዜ ገቢ በማሰባሰብና ድጋፋቸውን እያሳዩ ይገኛሉ፡፡
በዚህ የህብረተሰቡ ተሳታፊነት ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በጥራት ተሰርተው ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን እንደሚረዳም መገንዘብ ይቻላል፡፡
በኮይሻ ፕሮጀክት ሥር ያለው ሀላላ ኬላ ሪዞርት ባለፈው ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)ን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት መመረቁ ይታወሳል፡፡
ሪዞርቱ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በጥራት ተገንብቶ መጠናቀቁም የሚታወስ ነው፡፡
የፕሮጀክቱ ግንባታም የአካባቢው ማኅበረሰብ ነባር የኪነ-ህንፃ ጥበብን ከዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂ ጋር በማናበብ ማራኪ በሆነ አግባብ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ ይታወቃል፡፡
ሪዞርቱ በተገነባበት ሥፍራ የሚገኘው የጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ ሰው ሰራሽ ኃይቅ የሪዞርቱ ተጨማሪ ውበት መሆኑ ይጠቀሳል፡፡
በውስጡም ፕሬዚዳንታዊ የእንግዳ ማረፊያዎች፣ ዘመናዊ መኝታ ክፍሎችና ሌሎች የመዝናኛ ሥፍራዎችን የያዘ ነው፡፡
የሪዞርቱ መገንባትም ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ነው የተጠቆመው፡፡
ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ሃብት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስማቸው በቀዳሚነት የምትጠቀስ በመሆኗ በቱሪዝም መስኩ የምታደርገውን የማስተዋወቅና ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ ገና ብዙ ማድረግ የሚጠበቅባት እንደሆነ እሙን ነው፡፡
ሆኖም ኢትዮጵያ በገበታ ለሀገር መዳረሻዎች እየተገበረችው ያለቻቸው ፕሮጀክቶች የሚደነቁ እንደሆኑ ይነሳል፡፡