Fana: At a Speed of Life!

ለሰላም ሁሉም በጋራ በመቆም ወንጀልን መከላከል ይጠበቅበታል- ፌዴራል ፖሊስ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰላም የሁሉም ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ባለድርሻ አካላት ከፖሊስ ጎን በመቆም ወንጀልን መከላከል እንደሚጠበቅባቸው የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል አስገነዘቡ፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚሠሩ የሜትር ታክሲ ባለንብረቶች ጋር በፀጥታ ጉዳይ ላይ መክሯል፡፡

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት÷ ሰላም የሁሉም ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ባለድርሻ አካላት ከፖሊስ ጎን በመቆም ወንጀልን መከላከል ይጠበቅባቸዋል፡፡

የሜትር ታክሲ ባለንብረቶችም ከተለያዩ ሀገራት ተሞክሮ በመውሰድ በፀጥታ ዙሪያ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን አለባቸው ማለታቸውን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በቅርቡ የዜጎች የትስስር ማዕከል (ሲ ኢ ሲ) መተግበሪያን ሥራ ላይ እንደሚያውልም አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም የሜትር ታክሲ ባለንብረቶች ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጋር የቴክኖሎጂ ትስስር በመፍጠር በሜትር ታክሲ እየተፈፀሙ የሚገኙ ወንጀሎችን መከላከል እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

የሜትር ታክሲ ባለንብረቶች በሥራቸው በሚመዘገቡ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚያደርጉት ቁጥጥር የተዳከመ ስለሆነ ጠንካራ ቁጥጥር ሊያደርጉ እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ቀድመው ተመዝግበው ፈቃድ ለማሳደስ የሚቀርቡ እና አዳዲስ ተመዝጋቢዎችንም ያለ ፖሊስ ማረጋገጫ ማስተናገድ እንደሌለባቸው ነው ያሳሰቡት፡፡

የሜትር ታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ባለንብረቶች አሠራራቸውን በማዘመን ካሜራ እና ጂ ፒ ኤስ ገጥመው ቢጠቀሙ ለተገልጋይም ሆነ ለአሽከርካሪው ደኅንነት እንደሚበጅ መክረዋል፡፡

የወንጀል መከላከል ሥራውን ለማጠናከር በፖሊስ ተቋም በኩልም እያንዳንዱ የትራፊክ ፖሊስ አባላት በሥራ ወቅት ተንቀሳቃሽ ካሜራ ታጥቀው እንደሚሰማሩ ጠቁመዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.