በሚቀጥሉት ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ የቋሚ ተክሎችን የውኃ ፍላጎት ለማሟላት ይረዳል -ኢንስቲትዩቱ
አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚቀጥሉት አሥር ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ ቋሚና እድገታቸውን ያልጨረሱ ተክሎችን የውኃ ፍላጎት ለማሟላት እንደሚረዳ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለፀ።
ኢንስቲትዩቱ ዛሬን ጨምሮ ለቀጣይ አሥር ቀናት የሚኖረውን የአየር ሁኔታ ትንበያ ገልጿል።
በዚህም በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆነና ጥምር ግብርና የሚያካሂዱ የደቡብ፣ የደቡብ ምስራቅና የደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው እርጥበት እንደሚያገኙም ነው የጠቆመው።
ይህም ለቋሚና እድገታቸውን ላልጨረሱ ሰብሎች የውኃ ፍላጎት መሟላት ፤ በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ለሚካሄዱ የእንስሳት ልማት ስራዎች እንደሚጠቅም ትንበያው አመላክቷል።
የሚገኘው እርጥበት ለመጠጥ ውኃ አቅርቦት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም እንዲሁ።
በተጨማሪም በመካከለኛው በሰሜንና በሰሜን ምስራቅ አካባቢ የሚኖረው እርጥበት የበልግ እርሻ እንቅስቃሴን ቀድመው ለሚጀምሩ አካባቢዎች ማሳን አስቀድሞ ለማዘጋጀት ጠቀሜታው የጎላ ነው ተብሏል።
ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ፣ አርሲና ምዕራብ አርሲን ጨምሮ በቦረና ዞኖች፣ የሲዳማና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ኢዜአ ዘግቧል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አብዛኛው ዞኖች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙም ተጠቅሷል።
የላይኛውና መካከለኛው ዓባይ ስምጥ ሸለቆ፣ ኦሞ ጊቤ፣ የላይኛው ባሮ አኮቦ፣ ገናሌና ዋቢ ሸበሌ በጥቂት የላይኛው አዋሽና አፋር ደናክል ተፋሰሶች መጠነኛ እርጥበት እንደሚያገኙ ተመላክቷል።
በሌላ በኩል ደግሞ ተከዜ፣ ኦጋዴን፣ አዋሽ፣ ገናሌ ዳዋ ላይ ደረቅና ከፊል ደረቅ እንደሚሆኑ ተመላክቷል፡፡