Fana: At a Speed of Life!

በሙስና ወንጀል የተከሰሱት የቀድሞ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት የመረጃ ክትትልና ትንተና ቡድን መሪ አቤል ጌታቸው በጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የቀድሞ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት የመረጃ ክትትል እና ትንተና ቡድን መሪ አቤል ጌታቸው እና በግል ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ፉፋ ዳባ ጥፋተኛ በተባሉበት ድንጋጌ በእስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ ተወሰነ።

የቅጣት ውሳኔውን ያስተላለፈው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ሁለት ክሶችን አቅርቦ ነበር።

አቤል ጌታቸው በተባለው ግለሰብ ላይ የቀረበው ክስ ተከሳሹ የሙስና ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 1 እና ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተጠቀሰውን ድንጋጌ ተላልፏል የሚል ነው።

ሁለተኛ ተከሳሽን ፋፋ ዳባን በሚመለከት ደግሞ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ሕጋዊ አድርጎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ ፣ ስር ያለውን ድንጋጌ በመተላለፍ የሚል ክስ ነው የቀረበው።

አቶ አቤል ጌታቸው የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ውስጥ የመረጃ ክትትልና ትንተና ቡድን መሪ ሆነው ሲሰሩ የተቋሙን አሰራር ባልተከተለ መልኩ የባለሃብቶችንና የድርጅቶችን የባንክ ሒሳብ አስቀድሞ በማጥናትና መረጃ በመውሰድ በተለያዩ ጊዜያት ለባለሃብቶች ስልክ በመደወል በአካል በማግኘት ገንዘብ እንዲከፍሉ በመጠየቅ የማይከፍሉ ከሆነ ደግሞ የፋይናንስ እንቅስቃሴያቸውን በተመለከተ ለፖሊስ በማስተላለፍ የወንጀል ክስ እንደሚመሰረትባቸው በመግለጽ አስፈራርተዋል በማለት ነው ዐቃቤ ሕግ በክሱ የጠቀሰው።

በዚህ መልኩ ተከሳሹ በ2013 እና በ2014 ዓ.ም በተለያዩ ጊዜያት ባለሃብቶችን በማስፈራራት ከ3 ግለሰቦች 3 ሚሊየን 70 ሺህ ብር ገንዘብ ፉፋ ዳባ በተባለው 2ኛ ተከሳሽ ስም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘቡ ገቢ እንዲደረግ በማድረግ በዋና ወንጀል አድራጊነት ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ ሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦበት ነበር።

ሁለተኛ ተከሳሽ ፉፋ ዳባን በሚመለከት ደግሞ በወንጀል የተገኘ 3 ሚሊየን 70 ሺህ ብር የወንጀል ፍሬ መሆኑን እያወቁ የገንዘቡን ምንጭ ለመደበቅ በስሙ በባንክ የገባውን ገንዘብ በተለያዩ መጠን በመጠቀም ሕገ ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ የሚል ክስ በዐቃቤ ሕግ ቀርቦበታል።

በዚህ መልኩ ክሱ ለተከሳሾች የክስ ዝርዝሩ ደርሷቸው በችሎት በንባብ ተሰምቷል።

ከዚህም በኋላ ተከሳሾች የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ፍርድ ቤቱ በዐቃቤ ሕግ የቀረቡ አምስት የሰው ምስክሮችን ቃል እና የሰነድ ማስረጃ መርምሮ ተከሳሾቹ እያንዳንዳቸው በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።

ይሁንና ተከሳሾቹ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው መከላከል አለመቻላቸውን ጠቅሶ ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።

ፍርድ ቤቱ ከዚህም በኋላ የግራ ቀኝ የቀረቡ የቅጣት ማክበጃና የቅጣት ማቅለያ አስተያየቶችን መርምሯል።

በዚህም አንደኛ ተከሳሽ አቶ አቤልን በሚመለከት በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ በሰላም ማስከበር ረገድ እንዲሁም በበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ጨምሮ አጠቃላይ ያቀረበውን የቅጣት ማቅለያ አስተያየቶችን በወንጀል ሕግ አንቀጽ 86 እና በአንቀጽ 82 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) መሰረት አጠቃላይ 7 የቅጣት ማቅለያ አስተያየቶችን ፍርድ ቤቱ ይዞላቸዋል።

ሁለተኛ ተከሳሽ ፉፋ ዳባን በሚመለከት ደግሞ ለሕዳሴ ግድብ ያበረከቱትን የቦንድ ግዢ ጨምሮ አጠቃላይ 5 የቅጣት ማቅለያ አስተያየቶች ተይዞላቸዋል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ የቅጣት ማክበጃ አስተያየት ያቀረበ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ በዝቅተኛ ደረጃ በመያዝ አንደኛ ተከሳሽን በዕርከን 16 መሰረት በ3 ዓመት ጽኑ እስራትና በ1 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ወስኗል።

ሁለተኛ ተከሳሽ ፉፋ ዳባ ደግሞ በዕርከን 22 መሰረት በ5 ዓመት ከ 6 ወራት ጽኑ እስራት እና በ6 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ይግባኝ እንደሚጠይቅ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጿል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.