Fana: At a Speed of Life!

የአድዋ ድል ልዩ የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ነው-የተለያዩ ሀገራት ተወካዮች

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአድዋ ድል ጥንካሬ፣ ትብብር፣ የሀገር ፍቅር፣ መስዋዕትነት የተንፀባረቀበት ልዩ የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ነው ሲሉ በ128ኛ የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ላይ የተገኙ የተለያዩ ሀገራት ተወካዮች ገለጹ።

በኢትዮጵያ የአርመንያ አምባሳደር ሳሃክ ሳርግስያን÷ የአድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን እንዲሁም ለጥቁር ሕዝቦች ወሳኝ የድል ታሪክ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በአድዋ ድል ጥንካሬ፣ ትብብር፣ የሀገር ፍቅር፣ መስዋዕትነት የተንፀባረቀበት ልዩ የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ መሆኑን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ የዛምቢያ ኤምባሲ የፖለቲካና አስተዳደር አማካሪ ናዋ ሲቦንጆ÷ የአድዋ ድል ለአፍሪካ አህጉር ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያውያን ያለ ልዩነት ለሀገር ሉዓላዊነት በሕብረት የተሳተፉበት በመሆኑ የአንድነት ምሳሌ ነው ብለዋል።

በመሆኑም አፍሪካውያን የበለፀገችና አንድነቷ የተጠናከረ አፍሪካን ለመገንባት የአድዋ ድል ትምህርት የምንወስድበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የባንግላዲሽ ኤምባሲ የመከላከያ አታሼ ብርጋዴር ጄኔራል ጂኤም ሻሪፉል÷ የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝቦች መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያውያን በአንድነት የፋሽስት ወራሪን ኃይል ድል ያደረጉበት 128ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በአድዋ ድል መታሰቢያ በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.