Fana: At a Speed of Life!

ገዢው ፓርቲ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እየተወያየ መስራቱን እንደሚቀጥል ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ ገለፁ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 5 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከምርጫና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሰጠው የእፎይታ ጊዜ የወቅቱን ፈተና ለማለፍ ከማገዝ ባለፈ እንደ ሃገር ዴሞክራሲን መለማመድ እንድንችል አንድ እርምጃ ወደፊት የገፋ አጋጣሚ መሆኑን ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በምርጫና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከሰጠው የእፎይታ ጊዜ ጋር በተያያዘ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ኮቪድ19 አሁን ላይ የሚያስከትለው ጉዳት እየጨመረ መሆኑን ጠቅሰው ወረርሽኙ ለሁሉም የመጣ ከመሆኑ አንጻር በጋራና በሁሉም አቅጣጫ መዋጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አያይዘውም ወረርሽኙ በተለይም በክረምቱ ወቅት ከፍ ያለ ጉዳት ያደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ አንስተው፥ ወረርሽኙ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ለ6ኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ የሚደረገው ዝግጅት መስተጓጎሉን አውስተው አሁን ላይም ሃገር አቀፍ ምርጫው ውሳኔ ማግኘቱን አንስተዋል።

ህገ መንግስቱ በየአምስት አመቱ ምርጫ እንደሚካሄድ ይደነግጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ህገ መንግስታዊ አካሄድን ተከትሎ የቀረበለትን የህገ መንግስት ማሻሻያ ትርጉም ተመልክቶ ምላሽ ሰጥቷል ብለዋል።

በዚህ መሰረትም አሁን ያሉት የፌደራልና የክልል ምክር ቤቶች የወረርሽኙ ስጋት ተቀርፎ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ እንዲቀጥሉና ምርጫው ከ9 እስከ 12 ወር ባለው ጊዜ እንዲካሄድ ወስኗልም ነው ያሉት።

ሂደቱ የሃገራችን ዴሞክራሲ ራሱን በራሱ እያጎለበተ እንደሚሄድ ማሳያ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ክስተቱንም የወቅቱን ፈተና ከማለፍ ባሻገር እንደሃገር ዴሞክራሲን ለመለማመድ እንድንችል አንድ እርምጃ ወደፊት የገፋ ነው ብለውታል።

ማንኛውም ሃገራዊ ነገር ለህዝብ እንደሚደረግ አውስተውም፥ ምክር ቤቱ የሰጠው የእፎይታ ጊዜ ለፓርቲዎች ሳይሆን ውሳኔው ለህዝቡ ደህንነት የተላለፈ ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ምርጫው ምርጫውን ለማከናወን ሲባል በሚከወኑ ሁነቶች ምክንያት የሚፈጠርን አደጋ ለመቀነስ በማሰብ መራዘሙንም አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ እንዲያብብ እና ሀገራዊ መግባባት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ገዢው ፓርቲ በቀጣይ ጊዜያት በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እየተወያየ እና እየተመካከረ መስራቱን ይቀጥላል ብለዋል።

ምንም እንኳ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያየ አመለካከት ቢኖረንም ያለችን ሀገር አንድ በመሆኗ ለዚህች አንድ ሀገር ስንል በሰከነ፣ በሰለጠነና ነገን አርቆ በሚያይ በሳል ስሜት ውይይት እና ምክክር ማድረጋችንን አናቋርጥም ነው ያሉት።

በተለይም የሀገሪቱን መፃኢ ዕድሎች በሚወስኑ ዋና ዋና ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ እየደረሱ ነገሮችን ማስተካከል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አሁን የትኛውም ተግባር ለአንድ የተወሰነ አካል ተጠቅልሎ የሚሰጥበት ወቅት አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የኮሮናቫይረስ በኢኮኖሚው ዘርፍ ላይ እያሳደረ ያለውን ጫና የመቀነስ ተግባር የሁሉም ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በተጨማሪም የስራ ዕድል ፈጠራን መደገፍ፣ አዳዲስ የልማት እድሎችን መጠቀም፣ ግብርናው በተለየ መንገድ ሄዶ ምርታማነት እንዲጨምር ማስቻል፣ አምራች ኢንዱሰትሪው ከውጭ የሚገባውን ምርት መቀነስ እንዲችል አቅሙን እንዲጨምር ማድረግ እና አማራጭ የፋይናንስ ምንጮችን መፈለግ የእያንዳንዳችን የቤት ስራ በመሆኑ በሀሳብና በስትራቴጂ የበኩላችንን መወጣት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

ይህ ጉዳይ ሀገርን እንደ ሀገር ህዝብን እንደ ህዝብ ለማኖር የሚከናወን ሀገራዊ ስራ በመሆኑ ሁሉም የፖለቲካ ሀይሎች ሊሰሩበት የሚገባና ሀገሪቱን ከፈተና የሚያወጣ ምንገድ መሆኑን ሁላችንም መገንዘብ ይገባናል ብለዋል።

መጪውን ምርጫ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊ እና ተዓማኒነት ያለው ለማድረግ በጋራ በቂ ዝግጅት እያደረግን እንቆያለን ሲሉም ነው ያስታወቁት።

በዚህ ረገድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪክ ማህብራት፣ ከሀይማኖት ተቋማት፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከታዋቂ ሰዎች እና ከሌሎች የሚመለከታቸው ሰዎች ጋር ኮሮናን የመከላከሉ ስራን በማያውክ መንገድ እንሰራለን ብለዋል።

በመንግስት በኩል ይህንን አጋጣሚ ሀገር እና ህዝብን ለማዳን ግዳጅ እንደተሰጠው፣ ሀላፊነት እንደተጣለበት አድርጎ ይቀበለዋል፤ አንደገዢ ፓርቲ እንደተጨማሪ የሀላፊነት ጊዜ ያየዋል ነው ያሉት።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔንን ሁላችንም በዚህ መልኩ ከተቀበልን፣ ምክር ቤቱ የህዝብን ደህንነት በበቂ ሁኔታ ለማስጠበቅ በማለም እንዳሳለፋቸውአድርገን ካመንን ከፊታችን መልካም ተግባር የምንፈፅምበት ጊዜ ተዘርግቷል ብለዋል።

በመሆኑም ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የኢኮኖሚ ተዋንያን፣ የሀይማኖት መሪዎች፣ የሀገር
ሽማግሌዎች እና የሚመለከታቸው ገንቢ ተግባር የሚያከናውኑ አካላት ጋር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን በቁጥጥር ስር ለማዋል፣ ከፊትታችን የተጋረጠውን የኢኮኖሚ ቀውስ ከፍተኛ ጉዳት ሳያደረስ በብቃት ለመወጣት፣ ሊደቀን የሚችለውን ረሃብና የምግብ እህል እጥረት ለመቋቋም እና ከሉዓላዊነት ጋር የተገናኙ ጥቃቶችን በቁርጠኝነት ለመመከት እና መጪውን ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃና ተዓማኒ ለማድረግ በጋራ ለመስራት ጥሪ አቀርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.