Fana: At a Speed of Life!

ቻይና ለአፍሪካ አገራት ከሰጠችው ከወለድ ነፃ ብድር ውስጥ በፈረንጆቹ 2020 መገባደጃ ላይ ሊመለስ የነበረውን ሰረዘች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2012 (ኤፍ. ቢ. ሲ.) ቻይና ለአፍሪካ አገራት በፈረንጆቹ 2020 መገባደጃ ላይ የሚመለስ ከወለድ ነፃ የሆነ ብድርን መሰረዟን ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ አስታወቁ።

ትናንትና የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እና የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ የተሳተፉበት የቻይና-አፍሪካ ጉባኤ በቪዲዮ ተካሂዷል።

ኮቪድ-19ን መከላከል ላይ ባተኮረው በዚህ ጉባኤ ላይም ፕሬዚዳንት ሺ ቫይረሱን ለመዋጋት የአፍሪካና የቻይናን ትብብር ጠይቀዋል።

ሁለቱም ወገኖች የማህበረሰባቸውን ጤና በመገንባት እንዲሁም አጠቃላይ ስትራቴጂካዊና የትብብር አጋርነታቸውን ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ በጋራ መሥራት እንዳለባቸውም ነው የጠቆሙት፡፡

ፕሬዚዳንት ሺ በዚህ ወረርሽኝ የአፍሪካ ሀገራት ክፉኛ መጎዳታቸውን አንስተዋል።

በመሆኑም የቻይና የፋይናንስ ተቋማት የአፍሪካ ሀገራት ብድር ማግኘት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ተቀራርበው እንዲሰሩም ነው የጠየቁት።

የአፍሪካ ሀገራት ፍላጎትን ባከበረ መልኩም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በዓለም ጤና ድርጅት በኩል የጤና ድጋፍ ቻይና እንደምታደርግ አስታውቀዋል።

የኮቪድ-19 ለመከላከል የሚያስችል ክትባት ወደስራ በሚገባበት ወቅትም አፍሪካ ከማንም ቀድማ እንደምታገኝ አረጋግጠዋል።
የአፍሪካ የበሽታ መከላከል ማዕከል /ሲዲሲ/ ዋና መስሪያ ቤትንም በአዲስ አበባ እንደምትገነባ አስታውቃለች።

ምንጭ፦ ቢቢሲና ሲጂቲኤን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.