በትግራይ ክልል ለ2013 እና 2014 የትምህርት ዘመን ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና መሰጠት ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል በቀድሞ ስርዓተ ትምህርት የተማሩ በ2013 እና በ2014 የትምህርት ዘመን መፈተን የነበረባቸው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተፈታኞች ፈተና መስጠት ተጀመረ፡፡
ፈተናው በክልሉ መቐለ፣ አኽሱም፣ ዓዲ-ግራት እና ራያ ዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጠ ሲሆን÷ 54 ሺህ ተማሪዎች ፈተናውን ይወስዳሉ ተብሏል፡፡
ፈተናው ከሐምሌ 2 እስከ 12 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ እንደሚሰጥም የክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡
በክልሉ በቀድሞ ስርዓተ ትምህርት የተማሩና በ2013 እና በ2014 የትምህርት ዘመን መፈተን የነበረባቸው ተፈታኞች ፈተናቸውን በወረቀትና በበይነ መረብ እንደሚወስዱም ተጠቁሟል፡፡
ከትግራይ ክልል ውጪ በሁሉም ክልሎች እና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከነገ ሐምሌ 3 ጀምሮ እስከ ሐምሌ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ይሰጣል።