የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ያስፈልጋል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ጋር ውይይት አድርጓል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ እዉነቴ አለነ በውይይት መድረኩ እንዳሉት፤ የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ችግርን የመከላከል ስራ ለአንድ ተቋም የሚተው አይደለም።
ችግሩ ስለሚያስከትለዉ ጉዳት የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የምክር ቤት አባላት የክረምት ስራቸዉ አንዱ አካል አድርገዉ ሊሰሩበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እድሪስ በበኩላቸዉ የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመግታት በሚደረገዉ ጥረት የቋሚ ኮሚቴዉ አባላት የሚያደርጉት ድጋፍና ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል።
ባለሥልጣኑ ችግሩን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራር በመፍጠር የማህበረሰቡን ግንዛቤ የሚያሳድግ ሰፊ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
የቋሚ ኮሚቴዉ አባላት ባለሥልጣኑ ችግሩን ለመከላከል እያከናወነ ያለዉን ጥረት አድንቀዉ፤ ወደ መረጣቸው ማህበረሰብ ሲመለሱ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ እያስከተለ ያለውን ጉዳት በማስገንዘብ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ መልዕክት ማስተላለፋቸውን የባለስልጣኑ መረጃ አመልክቷል።