Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምእራፍ ለማሸጋገር የአካባቢያችንን ችግር በአካባቢያችን ሽማግሌዎች ለመፍታት የጋራ እንቅስቃሴ ላይ ነኝ – የሽማግሌዎች መማክርት

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምእራፍ ለማሸጋገር የአካባቢያችንን ችግር በአካባቢያችን ሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች በኩል ለመፍታት የጋራ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገር ሽማግሌዎች መማክርት አስታወቀ።

የመማክርቱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ከሌሎች የመማክርቱ ሀላፊዎች ጋር በመሆን ዛሬ በሰጡት መግለጫ መማክርቱ ከዓመት በፊት ከኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመሆን የሚታዩ ችግሮችን በባህልና ወጋችን መሰረት ለመፍታት የጋራ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውሰዋል።

ይህን ወደ መሬት ለማውረድም ከአምስት ወራት በፊት የየክልሉ ታላላቅ የሀገር ሽማግሌ ተወካዮችን ማካተት የተቻለ ሲሆን፥ ይህንን መሰረት አድርጎ ስራዎችን መስራት ጀምሮ ነበር ነው ያሉት።

ነገር ግን ብዙም መራመድ ሳይቻል የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመከሰቱ በሚፈለገው ፍጥነት መጓዝ እንዳልተቻለ አመልክተዋል።

ሆኖም ወረርሽኙ ከሰላምና አንድነታችን በላይ ስለማይሆን አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ወደ ስራችን ገንበተናል ብለዋል።

መማክርቱ በመጀመሪያው ዙር በህወሃትና ብልጽግና ፓርቲ መካከል ያሉ ልዩነቶችን ለመመልከት ባቀደው መሰረት ማክሰኞ ወደ ትግራይ ክልል እንዳመራና በዚያም ከህወሃት ከፍተኛ አመራሮች ጋር እንደመከረ ተናግሯል።

በምክክሩም የሰላምና አንድነት ጉዳይ የውዴታ ግዴታ በመሆኑ ሁሉም በሀላፊነት ሊቆምለት የሚገባ ጉዳይ ነው በሚለው መግባባት ላይ ተደርሷል።

ከዚህ ውጭ ግን የህወሃት አመራሮች በርካታ ጥያቄዎች እንዳላቸውና ያንንም ለመማክርቱ ያቀረቡ ሲሆን፥ በጋራ ተግናኝቶ ለመነጋገር ግን ዝግጁ መሆናቸውን ነግረውናል ብሏል።

መማክርቱ በአዲስ አበባም ከብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ጋር በህወሃት በኩል የተነሱ ጥያቄዎች ማቅረብን ጨምሮ በሰላምና አንድነት ጉዳይ እንዲሁም ተገናኝቶ መነጋገር በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ከስምምነት መድረስ ተችሏል ነው ያለው።

በዚህም መማክርቱ በሁለቱ አካላት መካከል ቀርቦ ያለመነጋገር እንጂ ቢነጋገሩ በልዩነት ውስጥ ተስማምቶ በጋራ መቀጠል የሚቻልበት እድል እንዳለ ለመገንዘብ ተችሏል ብሏል።

የመማክርቱ ምክትል ሰብሳቢ ሻለቃ አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ እና ፓስተር ዳንኤል ገብረስላሴ አሁን ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምእራፍ ለማሸጋገር የውስጥ አንድነት ወሳኝ በመሆኑ እስከ መጨረሻው ድረስ ይህን በጎ አላማ እንደሚያስቀጥሉት ተናግረዋል።

መማክርቱ በቀጣይ ከሁለቱም አካላት የሚወያዩበትን ሀሳቦች ተመልክቶ በአንድ ላይ ለውይይት እንደሚጠራና ወደ መፍትሄ መምጣት እንደሚቻል ተስፋ እንዳለው አመላክቷል።

ምክክሩ በህወሃትና በብልጽግና ፓርቲዎች ብቻ የሚያበቃ አይደለም ያለው መማክርቱ በቀጣይ በኦሮሚያና ሌሎች አካባቢዎችም ባሉ ልዩነቶች ላይ ምክክር እንዲደረግ ከዚያም ወደ መግባባት እንዲመጣ እሰራለሁ ብሏል።

 

 

በኃይለየሱስ ስዩም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.