ህብረተሰቡ ለግድቡ ግንባታ የሚያደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 9 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኅብረተሰቡ ለግድቡ ግንባታ የሚያደረገውን ድጋፍና አስተዋጽኦ አጠናክሮ መቀጠሉን የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የኮሮና ቫይረስ በሀገራችን ከተከሰተ ወዲህ እንኳን ከ190 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡንም ምክር ቤቱ ገልጿል።
የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኘኑት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አብረሃም ÷ግድቡን ለማገባደድ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ረገድ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን አስረድተዋል።
ለዚህም የ8100 ተሳትፎ አንዱ ማሳያ ነው ያሉት ኃላፊው÷የሰኔ ወር ሪፖርትን ሳይጨምር ከ8100፣ ከቦንድና ከስጦታ 668 ሚሊዮን በላይ ገቢ መሰብሰቡን ገልጸዋል ።
ምክር ቤቱ የቫይረሱ ስርጭት ያስከተለው ክልከላ ባቀደው ልክ ለመንቀሳቀስ እንዳላስቻለውም ጠቁሟል።
ይሁን እንጂ ኅብረተሰቡ በ8100 ላይ በመሳተፍ፣ ቦንድ በመግዛትና ስጦታ በመስጠት ግድቡን በመደገፍ ላይ እንደሚገኝ ኃላፊው ተናግረዋል።
በቀጣይም የኅብረተሰቡን ተሳትፎ የሚያሳድጉና ግንዛቤውን የሚያጎለብቱ ሥራዎች በሚዲያ ላይ እንደሚሠሩም ምክር ቤቱ አስታውቋል።
የ8100 እና የቦንድ ሽያጭም ተጠናክሮ እንዲቀጥል እቅድ መያዙንም አቶ ኃይሉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።