የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ በህዳሴው ግድብ ለሚያደርጉት ድርድር ስኬታማነት ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ለሚያደርጉት ድርድር ስኬታማነት ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡
በአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና የደህንነት ክፍል ተወካይ እንዲሁም የህብረቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፕ ቦሬል በህዳሴው ግድብ ዙሪያ መግለጫ አውጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም ሶስቱ ሃገራት ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ እያደረጉት ላለው ድርድር ስኬታማነት ህብረቱ ድጋፉን ያደርጋል ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ሃገራቱ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ሊሰሩ ይገባልም ነው ያሉት፡፡
ሃገራቱ ይህን ካደረጉም ህብረቱ እገዛ እንደሚያደርግና ይህም መተማመንን በመፍጠር ውጥረትን ለማርገብ እንደሚረዳም አውስተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የተፋሰሱ ሃገራት በኢንቨስትመንትና በውሃ ደህንነት ያላቸውን ግንኙነት ለማደስ እንደሚረዳቸውም አስታውቀዋል፡፡
ህብረቱም ደቡብ አፍሪካ በአሸማጋይነት ሶስቱ ሃገራት መግባባት ላይ እንዲደርሱ የምታደርገውን ጥረት እንደሚያበረታታም ገልጸዋል፡፡