በአዲስ አበባ የሚከናወኑ የፀጥታና ደህንነት ሥራዎች ምርጥ ተሞክሮዎች በቤይጂንግ ቀረቡ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽነሮች በቻይና ቤይጂንግ የሀገራት ዋና ከተሞች የህዝብ ደህንነት 2024 ጉባኤ ላይ በአዲስ አበባ የሚከናወኑ የፀጥታና ደህንነት ሥራዎች ምርጥ ተሞክሮዎችን ማቅረባቸው ተገለፀ።
ከአፍሪካና ከመላው ዓለም የተውጣጡ የ18 ሐገራት የፖሊስና የፀጥታ አካላት የተሳተፉበት የሀገራት የዋና ከተሞች የህዝብ ደህንነት 2024 ጉባዔ በቻይና ቤይጂንግ ተካሂዷል፡፡
በጉባዔው÷ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋውና የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽነር ዓለሙ መግራ ተሳትፈዋል፡፡
በጉባዔው ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው÷ አዲስ አበባ ፖሊስ የከተማውን ፀጥታና ደህንነት ለማረጋገጥ በተለይም የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር፣ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርንና ሌሎች ወንጀሎችን ከመቆጣጠር አንፃር የተከናወኑ ተግባራትንና የቴክኖሎጂ አጠቃቀሞችን በተመለከተ ተሞክሮ አቅርበዋል።
ፖሊስ በሪፎርም ስራዎቹ ያከናወናቸውን የቴክኖሎጂ እመርታዎች፣ ህገ-ወጥ ገንዘብን ህጋዊ አድርጎ የመጠቀም ወንጀልን ለመቀነስ የተሰሩ የቅድመ ወንጀል መከላከል ሥራዎችን፣ የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ምርጥ ተሞክሮዎችና በተለይም የሽብርተኝነት ወንጀልን ለመከላከል እየተከናወኑ የሚገኙ ውጤታማ ተግባራትን በገለጻቸው አቅርበዋል፡፡
ጉባዔው አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ሁሉን አቀፍ ተቀባይነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ምቹ መደላድልን የፈጠረ ከመሆኑም ባሻገር የአዲስ አበባ ሠላም ከተማዋ ለቱሪዝም መዳረሻነት ያላት ተመራጭነት ያስተዋወቀ ጉባዔ እንደነበረ ተገልጿል፡፡
ከጉባዔው ጎንለጎን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ከቻይና ምክትል የህዝብ ደህንነት ሺ ያንጁን ጋር አዲስ አበባ ፖሊስ ከቤጂንግ ፖሊስ ጋር ቀጣይ በሚኖረው የትብብር ግንኙነት ዙሪያ መወያየታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡