የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የማጠቃለያ መርሐ-ግብር በአዲስ አበባ ተከበረ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የማጠቃለያ መርኃ-ግብር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደረጃ ተከብሯል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ÷ ዛሬ ለ19ኛ ጊዜ የሚከበረውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በዓል በዓድዋ ድል መታሰቢያ ፓን አፍሪካንዚም አዳራሽ “ሀገራዊ መግባባት ለህብረብሄራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል ባማረና በደመቀ ሁኔታ አክብረናል ብለዋል፡፡
በበዓሉ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር እና የሁሉም ክልሎች አፈ ጉባኤዎች እንደተገኙም ገልጸዋል፡፡
የሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ ቤት፣ የኢትዮጵያውያን ሁሉ መናገሻ፣ የአፍሪካ ህብረት መዲና እና ሶስተኛዋ የዓለም ዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባችን የህብረብሄራዊ አንድነታችን ተምሳሌት መሆኗን በሚመጥን ልክ በዓሉ ተከብሯል ብለዋል፡፡