የአውሮፓ ህብረት ሀገራት መሪዎች ለድህረ ኮሮና ቫይረስ ማገገሚያ የ859 ቢሊየን ዶላር በጀት ላይ ከስምምነት ደረሱ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች ከ4 ቀናት ተከታታይ ስብሰባ በኋላ የድህረ ኮሮና ቫይረስ ማገገሚያ በጀት ዙሪያ ከስምምነት መድረሳቸው ተገለፀ።
የህብረቱ አባል ሀገራት መሪዎች ከስምምነት የተደረሱበት የበጀት ማዕቀፍ 859 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር (750 ቢሊየን ዩሮ) ሲሆን፥ ገንዘቡም የ27 የህብረቱ አባል ሀገራት በድጋፍ እና በብድር መልክ የሚለቀቅ መሆም ታውቋል።
በስምምነቱ መሰረትም 390 ቢሊየን ዩሮ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በከፍተኛ ደረጃ ለተጎዱ ሀገራት በድጋፍ መልክ የሚቀርብ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፥ በዚህም ማዕቀፍ ጣሊያን እና ስፔን ከፍተኛ ተቀባዮች ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ቀሪው 360 ቢሊየን ዩሮ ደግሞ ለአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት በዘቅተኛ የወለድ መጠን የሚቀርብ መሆኑም ታውቋል።
በበጀቱ ዙሪያ ሲደረግ በነበረው ውይይትም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በከፍተኛ ደረጃ በተጎዱ ሀገራት እና የበጀቱ ወጪ ከፍተኛነት ባሳሰባቸው ሀገራት መካከል ልዩነት ተፈጥሮ እንደነበረም ተነግሯል።
በአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች የተደረሰው የበጀት ስምምነት በቀጣይ በህብረቱ አባል ሀገራት ቴክኒካዊ ድርድሮች የሚጠብቁት ሲሆን፥ በመቀጠልም ለአውሮፓ ሀብረት ፓርላማ ቀርቦ የሚፀደቅ ይሆናል።
ስምምነቱ ታሪካዊና የህብረቱን አንድነት የሚያስጠበቅ ነው ሲሉ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮና የጀርመን መራሄተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ገልፀውታል።
ባሳለፍነው አርብ በቤልጂየም ብራስልስ የተጀመረው የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች ስብሰባ 90 ሰዓታትን ከፈጀ ውይይት ብኋላ ነው በስምምነት የተጠናቀቀው።
ይህም በአውሮፓውያኑ 2000 በፈረንሳይ ኒስ ከተማ ለ5 ቀናት ከተካሄደው ስብሰባ ቀጥሎ ረጅሙ ነው ተብሎለታል።
ምንጭ፦ bbc.com
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።