Fana: At a Speed of Life!

ከ5 ሚሊየን ብር በላይ እንዲመዘበር በማድረግ የሙስና ወንጀል የተከሰሱ በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የባንክ መመሪያና የአሰራር ስርዓትን በመጣስ ከደንበኛ ሂሳብ ከ5 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ ወጪ በማዘዝ እና በመመዝበር በከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱ 5 ግለሰቦች ከ4 እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ወሰነ።

ተከሳሾቹ 1ኛ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተፈራ ደግፌ ቅርንጫፍ ተጠባባቂ ተቀዳሚ ቅርንጫፍ ባንኪንግ መኮንን በረከት ሙሉ፣ 2ኛ በቅርንጫፉ ተጠባባቂ የውስጥ ተቆጣጣሪ ማርታ ሃይሉ፣ 3ኛ በንግድ ስራ ይተዳደራል የተባለው ተስፋ ገ/ስላሴ፣ 4ኛ ጌትነት አለማየሁ እና 5ኛ ሪያን ሰይድ ናቸው።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ2016 ዓ.ም በተከሳሾቹ ላይ ማለትም በአንደኛው ክስ በ1ኛ እና በ2ኛ ተከሳሾች ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀፅ 32 (1) (ሀ) እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 9 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) እና ንዑስ ቁጥር (2) ስር የተመላከተውን ድንጋጌ መተላለፍ የሚል ክስ አቅርቧል።

በሁለተኛው ክስ ደግሞ ከ3ኛ እስከ 5ኛ ተራ ቁጥር በተጠቀሱ ተከሳሾች ላይ ብቻ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) እና በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 780/200 5 አንቀጽ 29 ንዑስ ቁጥር 1 ሥር የተመለከተውን ድንጋጌ መተላለፍ የሚል ክስ አቅርቦባቸዋል።

በዚህ መልኩ በቀረበው በአንደኛው ክስ ላይ እንደተመላከተው 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጥቅምት 2013 ዓ.ም ያጸደቀው የቅርንጫፍ ባንኮች የአሰራር ስርዓት መመሪያ ደንብን በመተላለፍ የባንኩ ደንበኛ የሆኑት የግል ተበዳይ አቶ ይትባረክ ይኩኑ አምላክ ከሂሳብ ቁጥራቸው ላይ ገንዘብ ተቀናሽ ሆኖ ወደ ሌላ ሂሳብ እንዲተላለፍ ጥያቄ ባላቀረቡበት ሁኔታ ላይ ከደንበኛው ሂሳብ ያለአግባብ የገንዘብ ዝውውር ለመፈፀም እንዲያስችላቸው በባንኩ ተጥሎ የነበረውን የክልከላ ገደብ መተላለፋቸውን በክሱ ተጠቅሷል።

በዚህ መልኩ 1ኛ ተከሳሽ በባንኩ የተሰጠውን የሚስጥር ቁጥር ለ2ኛ ተከሳሽ አሳልፎ በመስጠት 2ኛ ተከሳሽ ደግሞ በመስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም ደግሞ ምንም አይነት ግብይት በሌለበት ሁኔታ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች የሆኑ ሰራተኞችን ኮምፒውተር በመጠቀም የደንበኛው የቀሪ ሂሳብ እና ፊርማ ምልከታ በማድረግ ፎቶ በማንሳት መረጃውን አሳልፋ ለሌላ የሰጠች መሆኑ ተመላክቷል።

በመስከረም 10 ቀን 2016 ዓ.ም ለጊዜው ማንነቱ ያልታወቀ ግለሰብ ከቅርንጫፉ ውጪ የተዘጋጁ እና በግል ተበዳይ ያልተፈረሙ ሁለት በሐዋላ ገንዘብ መላኪያ ቅጽ ይዞ በመቅረብ ለ1ኛ ተከሳሽ የሰጠው ሲሆን ተከሳሹም 4ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ደንበኞች እያስተናገደች የነበረችበትን ኮምፒውተር በመጠቀም ለ3ኛ ተከሳሽ ሂሳብ ቁጥር ብር 3 ሚሊየን 240 ሺህ ብር እና ለ4ኛ ተከሳሽ ደግሞ 2 ሚሊየን 160 ሺህ ብር በአጠቃላይ 5 ሚሊየን 400 ሺህ ብር ዝውውር ከፈፀመ በኃላ በራሱ የኮምፒውተር መጠቀሚያ ዩዘር ግብይቶችን ያፀደቀ መሆኑ በክሱ ተዘርዝሯል።

2ኛ ተከሳሽም ደግሞ ግብይቶችን ኦዲት በማድረግ ያረጋገጠች በመሆኑም በአጠቃላይ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የአሰራር ስርዓት መመሪያ በግልጽ ተግባር በመተላለፍ ደንበኛው ባልቀረቡበትና የክፍያ ጥያቄ ባላቀረቡበት ሁኔታ ከሂሳባቸው ገንዘብ ወጪ በማድረግ በባንኩ ላይ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ እና ለሌሎች ሰዎች ያልተገባ ጥቅም እንዲውል ያደረጉ መሆናቸው ተጠቅሶ ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት ስልጣንን አለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡

በሁለተኛው ክስ ደግሞ ከ3ኛ እስከ 5ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ተከሳሾች ላይ በቀረበው ክስ እንደተገለጸው፤ ተከሳሾች የንብረቱን ህገ-ወጥ ምንጭ ለመደበቅ እና ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ በማሰብ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድነት ቅርንጫፍ ደንበኛ ከሆኑት የግል ተበዳይ ከሂሳብ ቁጥራቸው ላይ ያለአግባብ ወጪ ከሆነው ብር ውስጥ በተለያዩ መጠኖች በተከፈተ ሒሳብ በማስተላለፍ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ተከሰዋል፡፡

ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ችሎት ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው ከተደረገ በኋላ በክሱ ዝርዝር የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ያቀረበ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ማስረጃዎችን መርምሮ የተጠቀሰው የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን መረጋገጡን ጠቅሶ ተከሳሾቹ በየደረጃው በተከሰሱበት ድንጋጌ ስር እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።

ሆኖም ተከሳሾቹ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው መከላከል( ማስተባበል) አለመቻላቸው ተጠቅሶ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮና ተከሳሾች ያቀረቡትን የቅጣት ማቅለያ አስተያየቶችን በመያዝ 1ኛ ተከሳሽን በ4 ዓመት ከ5 ወራት ጽኑ እስራት እና በ4 ሺህ ብር፣ 2ኛ ተከሳሽን በ4 ዓመት ጽኑ እስራትና በ3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ተወስኗል።

3ኛ፣ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾችን ደግሞ እያንዳንዳቸውን በ10 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ25 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ተወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.