ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የልማት ስራዎች ጉብኝት እንደቀጠለ ነው
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በክልሎች እያደረጉት ያለው የልማት ስራዎች ጉብኝት እንደቀጠለ ነው።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል የአዘዞ ጎንደር የአስፓልት የመንገድ ስራ ያለበትን ሂደት ተመልክተዋል።
እንዲሁም በጎንደር ከተማ በግብርናው ዘርፍ የተከናወኑ ያሉ የሌማት ትሩፋት ስራዎችን የጎበኙ ሲሆን÷በቀጣይም ሚኒስትሩና ሌሎች የሥራ ሀላፊዎች የፌደራል ፕሮጀክቶችን የሥራ እንቅስቃሴ ይጎበኛሉ።
በተጨማሪም የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ በጉብርዬ ክፍለ ከተማ የኢንዱስትሪ፣ የከተማ ግብርና እና ሌሎች የልማት ስራዎችን መጎብኘታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽም መረጃ ያመላክታል፡፡
እንዲሁም የመከላከያ ሚኒስትሯ አይሻ መሐመድ(ኢ/ር) ምስራቅ ዕዝ ያከናወናቸው እና እያከናወናቸው የሚገኙ የመሠረተ ልማት ስራዎች እና የዕዙ አጠቃላይ የግዳጅ አፈፃፀምን ተመልክተዋል።
አይሻ መሃመድ(ኢ/ር) በዚሁ ወቅት÷ምስራቅ ዕዝ በአነስተኛ በጀት በአጭር ጊዜ ያከናዋናቸው በርካታ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ለሌሎች ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጭምር ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና የፕላንና ልማት ሚኒሰቴር ከፍተኛ አመራሮች የአዲስ አበባ ከተማ የሱፐርቪዥን ድጋፍ ስራዎች በቂርቆስና በለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞች የተሰሩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የልማት ስራዎችን ተመልክተዋል፡፡
ሚኒስትሩ ጉብኝታቸው የሚዛን ቡና ቅምሻና ሰርትፊኬሽን ማዕከል፣ የሚዛን አማን ዱቄት ፋብሪካንና በግል ባለሀብት በግንባታ ላይ የሚገኘውን የሙፍቲ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን የስራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።
በተመሳሳይ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል ከፋ ዞን የልማት ስራዎች ጉብኝት በጊንቦ እና አዲዮ ወረዳዎች የመስከ ምልከታቸውን ቀጥለዋል፡፡
በምናለ አየነው