ኢራን ለኢትዮጵያ የማደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል አለች
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢራን በኢኮኖሚ፣ በቴክኖሎጂ እና በንግድ አማራጮች ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋገጠች፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ከኢራን የፓርላማ ልዑክ ጋር በሀገራዊና ፓርላሜንታዊ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ኢትዮጵያ እና ኢራን ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ በወዳጅነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አፈ-ጉባዔ ታገሰ አውስተዋል፡፡
ለአብነትም በ1960ዎቹ ኢትዮጵያ በኢራን ቆንፅላ መክፈቷንን ጠቅሰው÷ ኢትዮጵያ ከኢራን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ ትፈልጋለች ማለታቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡
በቀጣይም ሀገራቱ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አብረው በመሥራት ግንኙነታቸውን በይበልጥ ሊያጠናክሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የኢራኑ አፈ-ጉባዔ መሐመድ ጋሊባፍ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ሀገራቸው ኢትዮጵያ የጀመረችውን የኢኮኖሚ እድገት ለማጠናከር በኢኮኖሚ፣ በቴክኖሎጂ እና በንግድ አማራጮች በመደገፍ ወዳጅነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
ከውይይቱ በኋላ አፈ-ጉባዔዎቹ በምክር ቤቱ ቅጥር ግቢ አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል፡፡