በመዲናዋ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ 60 ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ገቡ
አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ስድስት ወራት በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ 60 ፕሮጀክቶች ወደ ስራ መግባታቸውን የከተማዋ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የኮሚሽኑ የእቅድና በጀት ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክተር ወ/ሮ አናትነሽ ታመነ÷ባለፉት 6 ወራት በመዲናዋ በተለያዩ ዘርፎች ለሚሰማሩ አልሚዎች አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
የአልሚዎችን ፍላጎት መሰረት በማድረግ የኢንቨስትመንት ለውጥ ማሻሻያ ሥራ መከናወኑን ጠቁመው÷ በዚህምለ192 ባለ ሃብቶች የኢንቨስትመንት ለውጥ ማሻሻያ ፈቃድ መሰጠቱን ጠቅሰዋል፡፡
በግማሽ ዓመቱ ለ1ሺህ 500 ባለሃብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ ለ1 ሺህ 303 አልሚዎች መሰጠቱንም አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩል በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ 60 ፕሮጀክቶች ወደ ስራ ገብተዋል ያሉት ዳይሬክተሯ÷248 ፕሮጀክቶች ከቅድመ ትግበራ ወደ ትግበራ መሸጋገራቸውን ጠቁመዋል፡፡
የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመንና ቀልጣፋ በማድረግ በለሃብቱ በኦን ላይን አገልግሎት እንዲያገኝ የተሰራው ሥራ 95 በመቶ መድረሱንም አረጋግጠዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ