ለፍጆታ ምርቶች መናር ምክንያት የሆነውን የንግድ ሰንሰለት ርዝማኔ ለመቅረፍ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለፍጆታ ምርቶች መናር ምክንያት የሆነውን የንግድ ሰንሰለት ርዝማኔና ህገ-ወጥ ግብይትን ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሚኒስቴሩ የንግድና ሸማቾች ጥበቃ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ሊቁ በነበሩ÷ የሰብል ምርት ዋጋ አርሶ አደሩ ጋር በግማሽ ያህል መቀነሱን እና ከዋጋ ግሽበት ጋር በተያያዘ ሸማቹ የሚያነሳቸው ቅሬታዎች ተገቢነት ያላቸው መሆናቸው ገልፀዋል፡፡
የችግሩ ምንጭ የሆኑ የግብይት ሰንሰለት ርዝማኔ ፣ ህገ-ወጥነትና የቁጥጥር ስርአት ችግር እና የአቅርቦት ችግሮች መሆናቸውን የጠቀሱት ስራ አስፈፃሚው÷ችግሩን ለመቅረፍ ከክልል እስከ ወረዳ ባሉ መዋቅሮች በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡
1 ሺህ 417 የሰንበት ገቢያዎችን ጨምሮ የሸማች ህብረት ስራ ማህበራት አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ጠቅሰው በቀጣይ የማህበራቱን ቁጥር ለመጨመር፣ ደረጃቸውን እንዲሁም የአቅርቦትና ጥራት መጠናቸውን ለማሳደግ እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡
በመሆኑም ሸማቹ ማህበረሰብ ከመደበኛ ገበያ በማህበራት በኩል የተሻለ ዋጋ መኖሩን አውቆ ግብይት እንዲያደረግም አሳስበዋል፡፡
የፋና ሬዲዮ የጋዜጠኞች ቡድንም ባደረገው ቅኝት በአብዛኛው አምራች አካባቢዎች ላይ የሰብል ምርት ዋጋ መቀነሱን ተመልክቷል፡፡
ቡድኑ በአዲስ አበባ እህል መጋዘኖች ያለውን አሁናዊ የዋጋ ዳሰሳ በተመለከተበት ወቅት ደግሞ አልፎ አልፎ በድርድር ትንሽ ቅናሽ ካደረጉ ነጋዴዎች በስተቀር አብዛኛዎቹ ጋር በተጋነነ ዋጋ እንደሚሸጥ ተመልክቷል፡፡
በማርታ ጌታቸው