Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ በፈረንጆቹ 2020 ከ100 ስመ ጥር አፍሪካውያን መካከል አንዱ ሆነው ተመረጡ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 22 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፈረንጆቹ 2020 ከ100 ስመ ጥር አፍሪካውያን መካከል አንዱ ሆነው ተመረጡ፡፡

ሪፒዩቴሽን ፖል ኢንተርናሽናል የተሰኘው ተቋም የፈረንጆቹ 2020 በተለያዩ የሙያ መስኮች ስመ ጥር የሆኑ 100 አፍሪካውያንን ዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡

በዚህ ዝርዝር ውስጥም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በመሪዎች ደረጃ አንዱ ሆነው ተካተዋል፡፡

የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ሺሴኬዲ፣ የላይቤሪያው ምክትል ፕሬዚዳንት ጀዌል ሃዋርድ፣ የዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ሃፊዝ ጋነምን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚሰሩ አፍሪካውያንም በዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱ ናቸው፡፡

ከዚህ ባለፈም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ፀሃፊዎች፣ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች እና የስራ እድል ፈጣሪዎችን ጨምሮ በበርካታ የሙያ ዘርፎች የተሰማሩ አፍሪካውያን ተካተውበታል፡፡

ኢትዮጵያዊው የአፍሪካ ዘላቂ ልማት ግብ ማዕከል ዳይሬክተር ጀኔራል የሆኑት በላይ በጋሻውም ከ100 ስመ ጥር አፍሪካውያን መካከል አንዱ ሆነው ተመርጠዋል፡፡

ከእርሳቸው ባለፈም ስራ ፈጣሪዋና የሶል ሬብልስ ባለቤት ቤተልሄም ጥላሁንም በቢዝነስ ስራ እድል ፈጠራ ዘርፍ በፈረንጆቹ 2020 ከ100 ስመ ጥር አፍሪካውያን መካከል አንደኛዋ ሆናለች፡፡

ታታሪነት፣ ግልጽነት እና ተፅዕኖ ፈጣሪነት በዝርዝሩ ለመካተት እንደ መለኪያ የቀረቡ መስፈርቶች ናቸው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.