በኦሮሚያ ክልል ባለፉት 12 ሰዓታት 327 ሚሊየን 399 ሺህ 570 ችግኞች ተተክሏል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል በአንድ ጀንበር ማለትም ከጠዋቱ 12 እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ 327 ሚሊየን 399 ሺህ 570 ችግኞች ተተክሏል፡፡
በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የተለያዩ የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም ህብረተሰቡ ተሳታፊ ሆነዋል።
በአንድ ጀንበር በመጀመሪያ በክሉ 304 ሚሊየን ለመትከል ታቅዶ የነበረ ሲሆን አፈፃፀሙ ከእቅዱ አንፃር ከ20 ሚሊየን በላይ ብልጫ አለው።
አቶ ሽመልስ አብዲሳ በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ወቅት ሀገሪቱ ካለችበት የድህነት አረንቋ ለመውጣት መንግስት ህብረተሰቡን በማሳተፍ ወደ ብልፅግና የሚሸጋገርበትን ስትራቴጂ በመንደፍ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
የዚህ እቅድ አካል የሆነው አረንጓዴ አሻራ የማኖር መርሀ ግብር የነገው ትውልድ ያለምንም ችግር ውሀ በማግኘት በመስኖ ማልማት እንዲችል እና በኢኮኖሚ አስተማማኝ ደረጃ ላይ እንዲደርስ በማለም የሚከናወን ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
በዘንድሮው አመት በመላው ሀገሪቱ ለመትከል ከታቀደው 5 ቢሊየን ችግኞች መካከል 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች በክልሉ እንደተዘጋጀ የኦሮሚያ ክልል እርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ሀላፊ አቶ ዳባ ደበሌ ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ሁሉም ዞኖችና ከተሞች በችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ላይ ለተሳተፉ ሰዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡