የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ከ3 ነጥብ 3 ቢሊየን በላይ ሆኖ የቀረበለትን የ2013 የክልሉ መንግስት በጀትን አፀደቀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ከ3 ነጥብ 3 ቢሊየን በላይ ሆኖ የቀረበለትን የ2013 የጋምቤላ ክልል መንግስት በጀትን አፀደቀ።
የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት 5ኛ የምርጫ ጊዜ 5ኛ የስራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤውን የክልሉን የ2013 ዓመታዊ በጀት በማጽደቅ፣ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን በማጽደቅና ሹመቶችን በመስጠት አጠናቋል።
ምክር ቤቱ በጉባኤው የክልሉን የ2013 በጀት ዓመት ዓመታዊ በጀት 3 ቢሊየን 377 ሚሊየን 653 ሺህ 415 ብር እንዲሆን አጽድቋል።
ከዓመታዊ በጀቱ 2 ቢሊየን 373 ሚሊየን 739 ሺህ 047 ብሩ ከፌዴራል መንግስት በሚገኝ ድጎማ የሚሸፈን ሲሆን፥ ቀሪው 1 ቢሊየን 3 ሚሊየን 914 ሺህ 368 ብር ደግሞ በክልሉ የውስጥ ገቢ የሚሸፈን ነው፡፡
ምክር ቤቱ በጉባኤው የ2012 የክልሉን መንግስት የስራ አፈጻፀም ሪፖርት በመመልከት ያፀደቀ ሲሆን፥ የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የክልሉን ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት የ2012 በጀት ዓመት የኦዲት ሪፖርት ተመልክቷል።
በጉባኤው የ5 ካቢኔ አስፈፃሚ አካላት ሹመት ለምክር ቤቱ የቀረበ ሲሆን፥ ምክር ቤቱም የቀረበውን ሹመት በመመልከት በሙሉ ድምፅ ማጽደቁን የጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
ምክር ቤቱ ከወረዳ እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ21 ዳኞች ሹመትን ሲያፀድቅ፤ 2 ዳኞችን በስነ ምግባር ምክንያት እንዲሰናበቱ የወሰነ ሲሆን የቋሚ ኮሚቴዎችን ሹመትም አጽድቋል።
በተጨማሪም የተለያዩ አዋጆችን ያፀደቀ ሲሆን የጋምቤላ ግብርና ምርምር ማቋቋሚያ አዋጅ፣ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የለሙና ወደፊት የሚለሙ ተፋሰሶች መወሰኛ ረቂቅ አዋጅ፣ የክልሉ ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅንና ሌሎችን መርምሮ አጽድቋል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።