የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ልዩ የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ነገ ያካሂዳል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ልዩ የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ነገ የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚያካሂድ አስታውቋል፡፡
ለጨረታ የሚቀርበው የውጭ ምንዛሪ መጠን 60 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን÷ ጨረታው ለሁሉም ባንኮች ክፍት እንደሚሆን ተመላክቷል፡፡
ባንኩ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መረጃ÷ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራምን ተከትሎ የኢትዮጵያ የውጭ ክፍያ ሚዛን በተለይም የወጪ ንግድ፣ ሐዋላና የካፒታል ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ መሻሻል ማሳየቱን አንስቷል፡፡
በተለይም ከቅርብ ወራት ወዲህ ወርቅን ወደ ውጭ የመላክ ብቸኛ ሥልጣን ላለው ብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው የወርቅ መጠን በመጨመሩ ምክንያት የባንኩ ዓለም አቀፍ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት እጅግ አበረታች መሆኑን ገልጿል፡፡
የብሔራዊ ባንኩ የውጭ ምንዛሪ ፍሰት መጨመር የሪፎርሙ ጥሩና አዎንታዊ ውጤት ቢሆንም የማዕከላዊ ባንኩን ጥብቅ የገንዘብ ዕድገት ፖሊሲና የዋጋ ንረት ግብ ስኬት በማያደናቅፍ መልኩ ሊተገበር እንደሚገባ ነው ያስገነዘበው፡፡
በመሆኑም ከባንኩ የወርቅ ግዥ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የገንዘብ አቅርቦት ዕድገት ለማገናዘብና በማዕከላዊ ባንኩ እጅ ካለው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከፊሉን ለግሉ ዘርፍ በመስጠት በገበያው ላይ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ለማሻሻል ባንኩ የተወሰነ የውጭ ምንዛሪ ለባንኮች በጨረታ ለመሸጥ መወሰኑን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቀጣይ ጊዜ የውጭ ምንዛሪ ገበያ ሁኔታን በቅርበት በመከታተል እንደ አስፈላጊነቱ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ሽያጮችን እንደሚያካሂድ ተጠቅሷል፡፡
ይህም የባንኩን የዋጋና የውጭ ኢኮኖሚ መረጋጋት ለማስፈን ያስቀመጠው ስትራቴጂያዊ ግብ አካል መሆኑን ነው የገለጸው፡፡
በመሆኑም ባንኮች በተቀመጠው መስፈርት እና የጊዜ ማዕቀፍ መሰረት በጨረታው እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል፡፡