በወታደራዊ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር መሥራት እፈልጋለሁ- ኒጀር
አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) በኒጀር ሪፐብሊክ መከላከያ ሚኒስትር ሌተናል ጀኔራል ሳሊፎ ሞዲ ከተመራ ወታደራዊ ልዑክ ጋር ተወያዩ፡፡
በውይይታቸውም በመተማማን ላይ የተመሰረተ አንድነት እና የጋራ ጥቅምን የሚያስጠብቅ ግንኙነት እስካለ ድረስ፤ አፍሪካ ለሌላው ዓለም ዓርአያ የማትሆንበት ምክንያት የለም ብለዋል ሚኒስትሯ፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን ችግር የሚፈታው በራሳቸው በአፍሪካዊያን ነው የሚል የፀና አቋም እንዳላትም አስገንዝበዋል፡፡
ሌተናል ጀኔራል ሳሊፎ ሞዲ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ናት፤ ሀገራችንም ሆነች አኅጉራችን አፍሪካ ችግር በገጠማት ጊዜ ሀገራት ነፃነታቸውን እንዲጎናፀፉ ዋጋ ከፍላለች ብለዋል፡፡
በውትድርና እና በፀጥታ ጉዳዮች ላይም የኢትዮጵያ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው እና በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያን ሠራዊት ልምድ እና የወታደራዊ ትምህርት ቤቶችን ተሞክሮ በመቅሰም የኒጀርን ዘመናዊ የውትድርና ተቋም መገንባት እንደሚፈልጉ መናገራቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ መረጃ አመላክቷል፡፡