ለብልጽግና መሰረት የሆነውን ሰላም መጠበቅ የጋራ ኃላፊነት ነው- ብልጽግና ፓርቲ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለብልጽግና መሰረት የሆነውን የሰላም ዕሴት መጠበቅ የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ብልጽግና ፓርቲ አስገነዘበ፡፡
ፓርቲው ሰላምን ሁላችንም አብዝተን እንፈልጋለን፤ ለብልጽግና መሰረት የሆነውን የሰላም ዕሴት መጠበቅ ብሎም ለዘላቂ ሰላም በጋራ መቆም ደግሞ የጋራ ኃላፊነት ነው ብሏል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ ያጋራው ሙሉ መረጃ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ሰላምን አብዝተን እንሻለን!
አንድ ሀገር ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብና የህዝቦችን የእለት ተእለት ኑሮ ለመቀየር ሰላም መሰረታዊ ነገር ነዉ። በግለሰብ ደረጃም ቢሆን ሰላም ከሌለ ወጥቶ መግባት፤ ሰርቶ መብላት፤ ወልዶ መሳም አይቻልም፡፡
ሰላም ለሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ለእንሰሳት፣ ለዱር እንሰሳት፣ ለዕፅዋት፣ ለጋራ ሸንተረሩ፣ ለወንዞችና ጅረቶችም እጅጉን አስፈላጊ ነው።
በአንፃሩ ደግሞ ጦርነት አውዳሚ፣ ጦርነት ገዳይ፣ ሀገር ያፈርሳል፣ ዜጎችን ሀገር አልባ ያደርጋል፣ ድህነትንና ኋላቀርነትን ያስፋፋል። የጦርነት ጥሩ፤ የሰላም መጥፎ የለም። ለዚህም ነዉ ሰላምን አብዝተን የምንሻዉ።
የዜጎቻችን መሰረታዊ ፍላጎት ሰላም፤ ልማት፤ ነፃነትና ዴሞክራሲ ነዉ። ለዚህ ነዉ የብልጽግና ፓርቲ ሰላም፤ ሰላም፤ ሰላም ለኢትዮጵያ፤ ሰላም ለዜጎቿ፤ ሰላም ለአፍሪካ፤ ሰላም ለአለም እያለ በየመድረኩ አብዝቶ የሚሰብከዉ።
ለዚህ ነዉ ሰላማዊ ትግል አሻፈረኝ በማለት ነፍጥ አንስተዉ የሸፈቱ ሃይሎችን እንኳ ሳይቀር ዛሬም ድረስ እጃችንን ዘርግተን ደጋግመን የሰላም ጥሪ የምናስተላልፈው። እንደ ፓርቲ የሰላም አማራጭ የምናስቀድመዉ ህዝባችን የባሩድ ሸታ ሳይሆን የሰላም አየር መተንፈስ አለበት፤ ለህዝባችን ልማት ይገባዋል፤ ህዝባችን የለዉጡ ትሩፋት ተቋዳሽ መሆን እንዳለበት ስለምናምን ነዉ፡፡
ብልፅግና ፓርቲ ለሰላም ያለዉ ቁርጠኝነት በብዙ ተግባሮች የሚገለፅ ነዉ፤ በሰሜኑ ጦርነት የወደሙ ተቋማት፤ መሰረተ ልማቶች እና ክልሉን መልሶ ለማቋቋም በበጀትም ሆነ በሌሎች ቁሳቁሶች መላዉን ኢትዮጵያዊያን በማስተባበር የተሄደዉ ርቀት ለሰላም ያለንን ቁርጠኝነት ለአለም ያሳበቀ ነዉ።
ፓርቲያችን በሁለተኛ መደበኛ ጉባኤዉ የተጀመረው አካታች ሀገራዊ ምክክር በስኬት ተጠናቆ የኢትዮጵያን የዘመናት የፖለቲካ ስንክሳር እንዲዘጋ፤ በልዩነትና በግጭቶች አያያዛችን ላይ ዘላቂ የመፍትሔ መንገዶች እንዲቀይስ፤ ለተጀመረው የሽግግር ፍትሕ ፕሮግራም ተግባራዊነትና ስኬታማነት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት፤ አዎንታዊ ዘላቂ ሰላማችንን እያስተጓጎሉ ከሚገኙ የታጠቁ ኃይሎች ጋር የሚደረገው ውይይትና ድርድር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አቅጣጫ ማስቀመጡ ለሰላም ያለንን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነዉ።
ኢትዮጵያ በብዙ ፀጋዎች የተሞሸረች እንዲሁም እድሜ ጠገብ ሀገር ሆና ሳለ በተለያዩ ጊዜያት በዉጭ ጠላቶችና በዉስጥ ባንዳዎች ሰላሟን አጥታ ፀጋዎቿን ተጠቅማ ወደ ብልፅግና ማማ መዉጣት አልቻለችም።
እነዚህ ምክንያቶች ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያን እየፈተኑ ቢገኙም እንኳን ትናንት አባቶቻችን በቋንቋ፤ በባህል፤ በሃይማኖት፤ በብሔር ሳይለያዩ አንድ ሆነዉ ወራሪዉን ፋሺስት ጣሊያን እና የዉስጥ ባንዳን ተዋግተዉ የጥቁሮች ሁሉ ድል የሆነዉን አድዋን አሸንፈዉ አለምን ጉድ እንዳሰኙ ሁሉ እኛም የአባቶቻችን ልጆች ስለሆን ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን አጠናክርን ኢትዮጵያና ህዝቦቿን የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ሁሉ በድል ተሻግረን ወደ ብልፅግና ሰገነት መዉጣታችን አይቀሬ ነዉ።
ሰላምን ሁላችንም አብዝተን እንፈልጋለን፤ ለብልጽግና መሰረት የሆነዉን የሰላም እሴት መጠበቅ ብሎም ለዘላቂ ሰላም በጋራ መቆም ደግሞ የጋራ ሃላፊነት ነዉ፡፡