በሀገር ውስጥ የመድሃኒት ምርትን ማሳደግ የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል ቁልፍ ነው – ዶ/ር መቅደስ ዳባ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገር ውስጥ የመድሃኒት ምርትን ማሳደግ የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል ቁልፍ ነው ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
ሚኒስትሯ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ጋር የሀገር ውስጥ የመድሃኒት ምርትን ማሳደግ በሚቻልበት መንገድ ዙሪያ ተወያይተዋል።
በውይይቱ በኢትዮጵያ የመድሃኒት ምርትን ለማሳደግ እና የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል የሚያስችሉ አስፈላጊ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችል ምክክር ተደርጓል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ ክትባት ለማምረት የሚያስችለው የሺልድቫክስ ፕሮጀክት ላይ ትኩረት ተደርጎ ምክክር መካሄዱን የጤና ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።
በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመድሃኒት አምራቾችን ለመሳብ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን በማዘጋጀት እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ እና የጋራ የቴክኒክ ቡድን በማቋቋም በትብብር ለመስራትም ቃል ተገብቷል።
ዶ/ር መቅደስ ዳባ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት፤ በሀገር ውስጥ የመድሃኒት ምርትን ማሳደግ የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል እና የውጭ ምንዛሬን ወጪን ለመቀነስ የሚያስችል ቁልፍ እርምጃ ነው።
ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በበኩላቸው በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመድሃኒት አምራቾችን ለመሳብ እና የሀገር ውስጥ የመድሃኒት ምርትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን እንደሚመቻቹ ተናግረዋል።