የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ በድህነት ላይ የተጎናጸፈችው ዳግማዊ ዓድዋ መሆኑ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ በድህነት ላይ የተጎናጸፈችው ዳግማዊ ዓድዋ መሆኑን የግድቡ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አመላከተ፡፡
ጽሕፈት ቤቱ ለ129ኛው የዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
ለግድቡ ግንባታ ከ21 ቢሊየን ብር በላይ ድጋፍ ከሕዝብ መሰብሰቡን ጽሕፈት ቤቱ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በላከው መግለጫ ገልጿል፡፡
ሕዝቡን በማስተባበር ግድቡ አሁን ለሚገኝበት ደረጃ ማድረስ መቻሉን የገለጸው መግለጫው፤ ፕሮጀክቱ ልጆቻችን በቅብብሎሽ የሚዘክሩት በድህነት ላይ የተከፈተ ሁለተኛው የዓድዋ ድል ገጽ መሆኑን አስገንዝቧል፡፡
በኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ያላሰለሰ ተሳትፎ መስዋዕትነት የተከፈለበት ፕሮጀክት መሆኑንም አመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ እንዳትለማ ጠላቶቿ ለዘመናት ቢጥሩም፤ በመንግሥትና ሕዝቡ ርብርብ የተፋሰስ ሀገራቱን የስምምነት ማዕቀፍ በማጽደቅ በቀጣናው የክፍለ ዘመኑን ከፍተኛ ድል አስመዝግባለች ብሏል፡፡
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት መላው የሀገራችንን ሕዝብ ብሎም የተፋሰስ ሀገራቱን ሕዝቦች በጋራ ለማደግ ፍላጎት ጥላ ሥር ያሰባሰበ፤ በቀጣናው የይቻላልን መንፈስ በተግባር ያረጋገጠ ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡
ፕሮጀክቱ በዜጎችና መንግሥት የነቃ ተሳትፎ የማጠቃለያ ምዕራፍ መድረሱን ያሳወቀው መግለጫው፤ አሁንም የሕዝብ ድጋፍና ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል፡፡