Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው – አቶ አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአማራ ክልል የኢንዱስትሪዎችን ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ በተጨማሪ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ፡፡

ንቅናቄው ከዚህ ቀደም ለኢንዱስትሪ ምርታማነት እንቅፋት የሆኑ ችግሮች በመቅረፍ መንግስትና ባለሃብቱ በቅርበት እንዲሰሩ ምቹ እድል መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ንቅናቄው የስራ እድል እንዲሰፋ እንዲሁም ሌሎች ለክልሉ እድገት አስተዋጽዖ የሚያደረጉ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ማድረጉን አመላክተዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ተከትሎ የገቢ ምርትን በመተካት ረገድ 324 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ ተኪ ምርት ማምረት መቻሉን አንስተዋል፡፡

እንዲሁም 50 ሺህ 772 የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ52 ሺህ 772 ዜጎች ሥራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል።

ለአምራቹ ዘርፍ የመሰረተ ልማት ጥያቄ የሆኑ የመብራት፣ የውሃና ሌሎች ጥያቄዎች በፍጥነት መልስ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ይህንንም ተከትሎ ምንም እንኳን በክልሉ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የጸጥታ ችግር ቢኖርም የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው እየጨመረ ባለሃብቱ በካፒታል መጠኑ እንዲያድግ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በአጠቃላይ የኢትየጵያ ታምርት ንቅናቄ ክልሉ በትክክል ያለውን ጸጋ እንዲያስተዋውቅ በማገዝ ውጤታማ እያደረገው ይገኛል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.