ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አገልግሎቶችን በማስፋት ስኬታማ ሆኛለሁ አለ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ባለፈው በጀት ዓመት አገልግሎቶችን እና ተደራሽነትን በማስፋፋት ውጤታማ አፈጻጸም ማስመዝገቡን ገልጿል፡፡
ተቋሙ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ፤ የአገልግሎት ተደራሽነትን በመጨመር፣ ቀጣይነት ያለው የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ በማድረግ፣ በማኀበረሰብ ነክ ጉዳዮች ላይ ከሕዝብ ጋር የሚያቀራርቡ ሥራዎችን በማከናወን ስኬታማ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዊም ቫንሄሌፑት፤ ያስመዘገብነው ስኬት በኢትዮጵያ መንግሥት፣ በተቆጣጣሪ አካላት፣ በባለአክሲዮኖቻችን እና በጠንካራ ቡድናችን ድጋፍ የተገኘ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በቴሌኮሙኒኬሽን እና በዲጂታል ክፍያ አገልግሎት ለማገዝ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
15 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በማዘዋወር በዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት አቅርቦት ጥሩ አፈጻጸም ማስመዝገባቸውንም ጠቁመዋል፡፡
የነዳጅ ክፍያ መፈጸም፣ ከውጭ ሀገራት የሚላክ ገንዘብን ማስተላለፍ እንዲሁም ከባንክ አገልግሎቶች ጋር በማስተሳሰር የአየር ሰዓት ግዢ እና የአገልግሎት ክፍያዎችን መፈጸም ማስቻል ለተመዘገበው ውጤት ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ መዝጊያ የተመዘገው ገቢ 7 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር መድረሱንም አንስተዋል፡፡
በትምህርት፣ ጤና እና ግብርና ፕሮጀክቶች ለማኅበረሰብ አገልግሎቶች ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለትምህርት ቤቶች ላፕቶፖችን እና ራውተሮችን ከ6 ወራት ነጻ የኢንተርኔት አገልግሎት ጋር ማበርከታቸውን ገልጸዋል፡፡