የልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ምርቶችን በጥራትና በፍጥነት ወደ ወደብ ለማድረስ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር አክሲዮን ማህበር የአንድ መስኮት አገልግሎት ማዕከል አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
ማዕከሉን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) እና የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) በዛሬው ዕለት አስጀምረዋል።
ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት÷ የአክሲዮን ማህበሩ የአንድ መስኮት አገልግሎት ማዕከል መጀመሩ በልዩ ዞኑ የሚገኙ ባለሃብቶችን የወጪና ገቢ ንግድን ለማሳለጥና የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት በኩል ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
ታከለ ኡማ (ኢ/ር) በበኩላቸው÷ የአንድ መስኮት አገልግሎት ማዕከል በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች የሚመረቱ ምርቶችን በተሻለ ፍጥነትና ጥራት ወደ ጅቡቲ ወደብ ለማድረስ የሚያስችል መሆኑን አመላክተዋል።
አገልግሎቱ በቀጣይም በሌሎች ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ይጀመራል ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ጳውሎስ በለጠ፤ ማዕከሉ በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የሚገኙ አልሚዎች ከኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር አክሲዮን ማህበር የሚፈልጉትን አገልግሎት በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።
ይህም ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን እንዲቆጥቡ የሚያደርግ መሆኑን ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።
አልሚያዎች ከተለያዩ ተቋማት ጋር የሚፈልጓቸውን አገልግሎቶች በቅርበት እንዲያገኙና ለሥራቸው ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ኮርፖሬሽኑ በትኩረት እየሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል።
በአድማሱ አራጋው