Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል 8 ሺህ 400 ዜጎች የኮደርስ ስልጠና እየተከታተሉ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከ8 ሺህ 420 በላይ ዜጎች የ5 ሚሊየን የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና መርሐ ግብርን እየተከታተሉ እንደሚገኙ የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ አስታውቋል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ግዛው ጋጊያብ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በክልሉ ከ138 ሺህ በላይ ዜጎችን በስልጠናው ለማሳተፍ ታቅዶ በትኩረት እየተሰራ ነው።

ዕቅዱን ለማሳካት ስለስልጠናው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እስከ ወረዳ ድረስ በመፍጠር ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመው÷በተለይም የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

እስካሁን ከ2 ሺህ በላይ ወጣቶች ስልጠናውን አጠናቅቀው የምስክር ወረቀት መውሰዳቸውን የተናገሩት ኃላፊው÷ በየጊዜው አፈጻጸሙን በመገምገም የክትትልና ድጋፍ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

ሥልጠናው ሲጀመር ከግንዛቤ ማነስ ጋር በተያያዘ በተፈለገው ልክ ዜጎች አለመሳተፋቸውን አንስተው÷ ይህም በአፈጻጸም ላይ የሚፈለገው ውጤት እንዳይመዘገብ ማድረጉን ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ በቀጣይ ከዕቅድ በላይ ለማሳካት በምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የሚመራ ስትሪንግ ኮሚቴ ተዋቅሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

በዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ የክልሉ ወጣት ተጠቃሚ እንዲሆንና በዘርፉ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ዕቅዱን ለማሳካት ከዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ጋር የድጋፍና ክትትል ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አመላክተዋል።

በአድማሱ አራጋው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.