Fana: At a Speed of Life!

ኢኖቬሽንን በመጠቀም የዘመናዊ ሠራዊት ግንባታን ማፋጠን ይጠበቅብናል – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢንተርፕሪነርሺፕ እና የኢኖቬሽን አቅሞቻችንን ተጠቅመን የዘመናዊ ሠራዊት ግንባታን ማፋጠን ይጠበቅብናል ሲሉ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
የመከላከያ ኢንተርፕሪነርሺፕ እና የኢኖቬሽን ማዕከል የምስረታ መርሐ ግብር እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ በመርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ከለውጡ ወዲህ በመከላከያ ሠራዊት በተለያዩ መስኮች በተሰሩ ከፍተኛ የሪፎርም ሥራዎች ዘመኑን የዋጀ ትጥቅ እንዲኖረው ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
መከላከያ የፖለቲከኞች መጠቀሚያ ሳይሆን ተልዕኮውን ብቻ የሚፈጽምና በአስተሳሰብም ጭምር ጠንካራ እንዲሆን ለማድረግ በተሰሩ ሥራዎች ውጤት እየተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።
በሠራዊቱ ኢትዮጵያን የሚመስል ስብጥር እንዲኖር መደረጉን የገለጹት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ በጤና፣ በሎጀስቲክስ፣ በመረጃ፣ በኢንዱስትሪ፣ በትምህርት መስኮች በተከናወኑ ጠንካራ የሪፎርም ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።
የኢንተርፕሪነርሺፕ እና የኢኖቬሽን ማዕከል ምስረታ ለተቋሙ የሪፎርም ሥራዎች ውጤታማነት አንዱ ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል።
ማዕከሉ ላለፉት ዓመታት የተለያዩ ሀገራት ሲተገብሩት የቆዩና ኢትዮጵያ ግን ያልታደለችበት አበረታች ጅምር መሆኑን ገልጸው፥ የመከላከያን አቅም በማጠናከር የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ከማሳደግ አንፃር ሚናው ከፍ ያለ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ለተሰዉና ቋሚ ተጧሪ ለሆኑ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያት ከሠራዊቱ ለወጡ አባላት ጭምር ተስፋ የሆነ ማዕከል በመሆኑ ለሀገር ኢኮኖሚና ለአስተማማኝ ሰላም የራሱን ድርሻ የሚጫወት መሆኑንም ገልጸዋል።
በምስረታ መርሐ ግብሩ ላይ የመለከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ (ኢ/ር)፣ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል እንዲሁም የሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮችና የቀድሞ አባላት ተሳትፈዋል።
በታምራት ደለሊ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.