ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከፔይትሮ ሳሊኒ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከ ‘Webuild Group’ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፔይትሮ ሳሊኒ ጋር በሮም ከተማ ተወያዩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መረጃ፤ በጥቂት ወራት ውስጥ በሚጠናቀቀው የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ኩራት በሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ እንዲሁም በኮይሻ ግድብ ፈጣን አፈፃፀም እንደታየው ሀገራዊ ግቦቻችንን በማሳካት ረገድ ከ ‘Webuild Group’ ጋር ያለን ትብብር ወሳኝ ነው ብለዋል።
በዛሬው ውይይታችንም፤ በመሠራት ላይ ባሉት ፕሮጀክቶች አፈፃፀም፣ በፍጥነት በታገዘ ውጤታማነት ላይ ፈጠራን እና ዘላቂነትን የሥራዎቻችን ማዕከል አድርገን መያዝ እንደሚገባ ተነጋግረናል ነው ያሉት፡፡
ውይይታችን የኢኮኖሚ እድገትን በመምራት እና የረጅም ጊዜ ልማትን በመደገፍ ሀገር የሚያሻግሩ ፕሮጀክቶችን በመከወን ረገድ ያለንን የጋራ ቁርጠኝነት ያንፀባረቀ ነበር ብለዋል።