በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በበልግ እርሻ ከ840 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በዓመታዊ ሰብል ተሸፍኗል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በበልግ እርሻ በአዝርዕትና ሆልቲካልቸር በዓመታዊ ሰብሎች 777 ሺህ 627 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ከ840 ሺህ 584 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
በቢሮው የእርሻ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አድማሱ አወቀ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በዘንድሮ የበልግ እርሻ ወቅት በተሰራው ሥራ ከዕቅድ በላይ አፈፃፀም ተመዝግቧል።
ከበልግ እርሻ ውስጥ 158 ሺህ 782 ሄክታር የአዝርዕት ሰብል በክላስተር ኩታ ገጠም እርሻ ታርሶ በዘር መሸፈኑን ገልጸው÷ በተመሳሳይ የሆልቲካልቸር ልማት 57 ሺህ 263 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም አርሻ እየለማ መሆኑን አመላክተዋል።
በክልሉ ለሜካናይዜሽን አመቺ በሆኑ አካባቢዎች በትራክተር 149 ሺህ 546 ሄክታር መሬት መታረሱን ገልጸው÷ በዚህም 196 ሺህ 205 አርሶ አደሮች ተሣታፊ እንደሆኑ ጠቁመዋል።
በምርት ዘመኑ የአዝርዕትና ሆልቲካልቸርን ጨምሮ ከቋሚና ዓመታዊ ሰብሎች 77 ሚሊየን 706 ሺህ 457 ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡
የሚጠበቀውን ምርት ለማግኘት የአርሶ አደሩን የግብዓትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም በማሻሻል እና የኩታ ገጠም እርሻን በማስፋት አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወኑን ተናግረዋል።
ለአርሶ አደሩ ከሰብል እንክብካቤ እንዲሁም ሊከሰት የሚችለውን ተምችና ተባይ ቀድሞ ከመከላከል አንጻር ተገቢ ሙያዊ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑንም አመላክተዋል።
በአድማሱ አራጋው