Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያና ዩክሬን የጦር እስረኞችን ለመለዋወጥ ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሩሲያ እና ዩክሬን የሚያደርጉት ሁለተኛ ዙር የሰላም ንግግር በቱርክ ኢስታንቡል ከተማ ተካሂዷል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገው ሁለተኛው ዙር የሰላም ድርድር የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን የመሩት ሲሆን÷ የቱርክ፣ ሩሲያ እና ዩክሬን ባለስልጣናት ተሳትፈውበታል።

የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን አማካሪ ቭላድሚር ሜዲንስኪ እና የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ሚካሂል ጋሉዚን ጨምሮ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት ሩሲያን ወክለው በሰላም ንግግር መድረኩ ተገኝተዋል።

በዩክሬን በኩል የመከላከያ ሚኒስትር ሩስቴም ኡሜሮቭ እና የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ሰርጊ ኪስሊቲት እንዲሁም የደህንነት ባለስልጣኖች ተሳታፊ ሆነዋል።

ከዩክሬን በኩል የቀረበውን የሰላም ሀሳብ ሰነድ ሩሲያ ስለመቀበሏ ሜዲንስኪ ያረጋገጡ ሲሆን÷ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ግን ሩሲያ ያቀረበችው ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

በሰላም ንግግሩ ሩሲያና ዩክሬን የጦር እስረኞችን ለመለዋወጥ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተጠቁሟል፡፡

ሁለቱ ወገኖች በፈረንጆቹ ሜይ 16 በዚሁ ቱርክ ውስጥ ተገናኝተው መነጋገራቸው ይታወሳል።

በወቅቱም በእስረኞች ልውውጥ እና የሰላም ንግግሮችን ማስቀጠል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተስማምተው ሁለቱ ሀገራት የእስረኞች ልውውጥ ማድረጋቸው ይታወቃል።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.