ሕጻናት የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ እንዲሆኑ የሚከናወኑ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕጻናት የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ እንዲሆኑ የሚከናወኑ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ አሉ የአስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
35ኛው የአፍሪካ ሕጻናት ቀን በአዲስ አበባ ከተማ በሴቶች አደባባይ በተለያዩ የሕጻናት ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ተከብሯል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ÷ የነገ ሀገር ተረካቢ ሕጻናትና የመጪው ዘመን ተስፋዎች ላይ በትኩረት መስራት የነገ ሕይወት መንገድን ለማቅናት ያስችላል ብለዋል፡፡
የሕጻናቱ የነገ እድገት እዳ የሌለበትና ለትውልድ የሚተርፍ እንዲሆን በትብብር እንደሚሰራ ጠቁመው ÷ ለዚህም የቀዳማይ ልጅነት መርሐ ግብር አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ሕጻናት ለሀገር ያላቸው ተስፋ እውን እንዲሆን ከማሕጸን ጀምሮ አስፈላጊውን እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡
በአዲስ አበባ ሕጻናት እየተጫወቱ ቁም ነገር የሚጨብጡባቸው እንዲሁም በአካልና አዕምሮ የሚጎለብቱባቸው ሥፍራዎች እየተገነቡ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
ዛሬ ላይ ሕጻናትን የሚያንጹ ተግባራትን ማከናወን የነገዋን ኢትዮጵያ በሚፈለገው መንገድ ለመገንባት ሚናው ጉልህ እንደሆነ መናገራቸውንም የከንቲባ ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ ሚኤሳ ኤሌማ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡
34ኛው የአፍሪካ ሕጻናት ቀን”የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለማነጽ ሕጻናት ተኮር ተግባራትን እናከናውን” በሚል መሪ ሃሳብ ነው የተከበረው፡፡
በዮናስ ጌትነት