Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ያልተቋረጠ ጥረት ያስፈልጋል – አምባሳደር ኤቭጌኒ ተረክኺን

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ያቀረበችው የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ያልተቋረጠ ጥረት ያስፈልጋል አሉ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኤቭጌኒ ተረክኺን፡፡

አምባሳደሩ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ ፥ እያደገ ለመጣው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ አማራጭ ዕድሎች የግድ እንደሚያስፈልጉ አንስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኢኮኖሚም ሆነ አጠቃላይ የእድገት ምጣኔ በዓለም አቀፍ ተቋማት የተመሰከረለትና የሚታይ ውጤት መምጣቱን ነው ያስረዱት።

የተገኘውን ውጤት ይበልጥ ለማሳደግና ደህንነቷን ለማስጠበቅ ያነሳችው የባሕር በር ጥያቄ ተገቢ ምላሽ እንዲያገኝ ያልተቋረጠ የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚስፈልግም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

እያደገ የመጣው የኢትዮጵያ እና ሩሲያ ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች ውጤት እያስገኘ ነው ያሉት አምባሳደሩ፥ በትምህርት፣ ኢኮኖሚ፣ ቴክኖሎጂ እና በኒውክሌር ሳይንስ ዘርፎች ያለውን ትበብር በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

በተያዘው ዓመት ብቻ የመንግስትን ቀጥተኛ የትምህርት እድል ጨምሮ 300 የሚደርሱ ተማሪዎች ወደ ሩሲያ ማቅናታቸውን ተናግረዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ትብብር በመሪዎቹ ወዳጅነት የተረጋገጠ መሆኑን ጠቅሰው ፥ እንደ ብሪክስ ባሉ ተቋማት ጭምር ማሳያ ሆኖ የሚቀርብ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቆይታቸው ባለፉት ሰባት ዓመታት የተመለከቱት በመንግስትና ሕዝብ መካከል የሚደረጉ ተከታታይ ውይይቶች ለሀገር እድገት በጋራ ለመቆም እንደሚረዱም አስገንዝበዋል።

በአሸናፊ ሽብሩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.