“የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት አዋጅ የዜጎችን መብትና ጥቅም የሚያስከብር ነው” ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል የተሻሻለው የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት አዋጅ ለሥራ ወደ ውጭ የሚሰማሩ ዜጎችን መብትና ጥቅም በተሻለ መልኩ የሚያስከብር ነው አሉ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ ሥራ ስምርትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ረቂቅ አዋጅ ላይ ይፋዊ የሕዝብ ውይይት አካሂዷል።
ሚኒስትሯ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ አዋጁ ከዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ መርህ ጋር የሚጣጣም እና ለሥራ ወደ ውጭ ሀገር የሚሰማሩ ዜጎች ክብርና ጥቅም እንዲጠበቅ ለማድረግ ያለመ ነው።
ወደ ውጭ ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎች ተገቢውን ክህሎት እንዲጨብጡ ለማድረግና በመስኩ የሚከናወኑ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን በተሻለ መልኩ ለመቆጣጠር እንደሚያስችል አመልክተዋል።
አዋጁ በሕጋዊ መንገድ ዜጎችን የሚልኩ ኤጀንሲዎች የተሻለ አቅም እንዲፈጥሩ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመው÷ የሥራ ፈላጊ ምዝገባ፣ ምልመላና ምደባ ሥርዓቱን እንደሚያጠናክርም አብራርተዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዳንኤል ተሬሳ በበኩላቸው÷ አብዛኛው ኤጀንሲዎች የሚንቀሳቀሱት አዲስ አበባ ላይ በመሆኑ በክልሎች አከባቢ ያለውን የስራ ፈላጊ መልምሎ የስራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ ላይ ክፍተቶች መኖራቸው በጥናት መለየቱን ተናግረዋል።
ክፍተቱን ለመሙላት ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሰራተኛ ምልመላና ምደባ ስራውን እንዲያከናውን በአዋጁ መደንገጉን አስረድተዋል።
በሰራተኛ ምልመላ ላይ የደላሎች ተሳትፎ መበራከት ሌላው ችግር መሆኑን በጥናት መለየቱን ጠቁመው÷ የደላላ ሰንሰለትን መቁረጥ አዋጁ ያስፈለገበት ሌላው ምክንያት መሆኑን አብራርተዋል።
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሕግ አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ ሲቲና መንግሥቱ ፥ አንድ ኤጀንሲ ፈቃድ ባወጣ በ6 ወር ውስጥ ሰራተኛ ወደ ውጭ መላክ እንዳለበት በአዋጁ መደንገጉን መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ይህም በህጋዊነት ሽፋን ሊደረጉ የሚችሉ ሕገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከል ያለመ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ፥ ዜጎች ለሥራ ብቁ የሚያደርጋቸውን ክህሎት ሳይወስዱ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ እንዳይወጡ በጋራ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።