Fana: At a Speed of Life!

አረንጓዴ አሻራ የተሻለ የዝናብ መጠንና የግብርና ምርታማነት እንዲኖር አስችሏል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ሳታቋርጥ እየተገበረችው ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ያደገ የዝናብ መጠንና የግብርና ምርታማነት ተመዝግቧል አሉ ምሁራን።

መርሐ ግብሩ የተስተካከለና ዘላቂነት ያለው ሥነ ምህዳር እንዲፈጠር ከማድረግ በተጨማሪ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ ያደረጉ ምሁራን ተናግረዋል።

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ የተፈጥሮ ሀብት አያያዝ ትምህርት ክፍል መምህር ካሳሁን ሙላቱ እንዳሉት፥ አረንጓዴ አሻራ የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባሻገር የግብርና ምርታማነትን ለመጨመርና የአየር ንብረት ለውጥ ጫናን ለመቋቋም የጎላ ድርሻ አበርክቷል።

መርሐ ግብሩ በዓለም አቀፍ የብዝሀ ህይወት ጥበቃ እንዲሁም የሀገሪቱን የልማት ዕቅድ በማሳካት ረገድ የጎላ ሚና አለውም ነው ያሉት።

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪ ሀርቆ ሀላላ በበኩላቸው፥ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ያደገ የዝናብ መጠንና እየጨመረ የመጣ የግብርና ምርታማነት እንዲኖር አስችሏል።

ከዚህም ባለፈ የተስተካከለና ዘላቂነት ያለው ሥነ ምህዳር እንዲፈጠር ማስቻሉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እገዛ እንዳለው ነው ያመለከቱት።

በቀጣይ ለሀገር በቀል ዝርያዎች በቂ ድርሻ መስጠት፣ የተጎዱ መሬቶችን በአግባቡ መለየት፣ የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብና በየደረጃው ይህንን የሚከታተሉ የማህበረሰብ ኮሚቴ የማደራጀት ሥራ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ምሁራኑ ጠቁመዋል፡፡

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሀገር ለማግኘት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ላይ የድርሻውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

በአስጨናቂ ጉዱ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.