የኦሮሚያ ክልል የ2018 በጀት 400 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ሆኖ ፀደቀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጨፌ ኦሮሚያ 400 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ሆኖ የቀረበለትን የክልሉን የ2018 በጀት አጽድቋል፡፡
ጨፌ ኦሮሚያ በ6ኛ የስራ ዘመን 4ኛ ዓመት 9ኛ መደበኛ ጉባዔ ሁለተኛ ቀን ውሎው የክልሉን የ2018 በጀት እና የ2017 ተጨማሪ በጀት እንዲሁም የተለያዩ ሹመቶችን አጽድቋል፡፡
በዚህም መሰረት የ2018 በጀት 400 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ሆኖ የፀደቀ ሲሆን፥ ይህም ከአምናው አንፃር በ40 ነጥብ 52 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ተጠቁሟል፡፡
በተመሳሳይ የክልሉን የ2017 በጀት ዓመት ተጨማሪ በጀት 30 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በማድረግ ማፅደቁም ነው የተገለጸው፡፡
ተጨማሪ በጀቱ በክልሉ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችንና አገልግሎቶችን ከዳር ለማድረስ የሚውል ነው፡፡
በሌላ በኩል ጨፌ ኦሮሚያ ወ/ሮ መሰረት አሰፋ የክልሉ የመሬት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም የሺ ጂማ (ዶ/ር) የክልሉ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አድርጎ ሹመታቸውን አፅድቋል።
ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የጨፌ ኦሮሚያ 6ኛ የስራ ዘመን 4ኛ ዓመት 9ኛ መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ በዛሬው ዕለት ተጠናቋል፡፡
በጸሀይ ጉልማ