Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በቡናው ዘርፍ መሰረታዊ ለውጥ አስመዝግባለች – ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በቡናው ዘርፍ መሰረታዊ ለውጥ አስመዝግባለች አሉ የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፡፡

በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣንና ሌሎች አጋር አካላት ትብብር የተዘጋጀውና በአፍሪካ የቡና እድገትና ለውጥ ላይ ያተኮረው የውይይት መድረክ ከ2ኛው የተባበሩት መንግስታት የምግብ ስርዓት ጉባኤ ጎን ለጎን እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ የ10 ዓመት የቡና ስትራቴጂን ተግባራዊ እያደረገች መሆኑን ጠቅሰው፥ በዘርፉ መሰረታዊ ለውጥ አስመዝግባለች ብለዋል፡፡

በስትራቴጅው ባለፉት አምስት አመታት መሰረታዊ ለውጥና እድገት መመዝገቡን ያነሱት ሚኒስትሩ፥ በዚህ አመት ከቡና የወጪ ንግድ የተገኘው የ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለቡና ውጤታማነት ትልቅ ሚና ተጯውቷልም ነው ያሉት፡፡

በኢትዮጵያ ከ 2ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የቡና ምርትን በቀጥታ ወደ ውጭ ገበያ እየላኩ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ይህም የቡናን የውጭ ንግድ ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ዘርፉን ለማሳደግ በሰራችው ስራ በዓመት በሄክታር ይገኝ የነበረውን 9 ቶን ምርት ወደ 29 ቶን ከፍ በማድረግ ዓመታዊ የምርት መጠኑን ወደ 5 መቶ ሺህ ቶን አድርሳለች ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከ8 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ቡናን በመትከል የማይበገር ኢኮኖሚን ለመገንባት እየሰራች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የቡናን ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ እሴት መጨመር፣ ጥራትን ከፍ ማድረግ፣ የውጭ ንግድን ማሳደግ፣ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግና ዲጂታላይዜሽንን በመጠቀም የግብይት ሰንሰለቱን ማዘመን ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ምክትል ዋና ፀሃፊ አሚና መሀመድ በበኩላቸው የአረቢካ ቡና ባለታሪክና ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ችግሮችን በመዋጋት በአግባቡ እየተጠቀመችበት ትገኛለች ብለዋል::

የቡናው ዘርፍ በዓለም ገበያ ላይ በቀጥታ ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያው ጥቅም ባሻገር በስራ ዕድል ፈጠራ የዜጎችን አኗኗር ዘይቤ የሚያስተካክል መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

በሰማኸኝ ንጋቱ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.