በመጪው ሐሙስ በጋራ ታሪክ እንስራ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመጪው ሐሙስ በጋራ ታሪክ እንስራ ሲሉ ጥሪ አቀረቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ በዚህ ሳምንት ኢትዮጵያ አረንጓዴ እና ለፈተና የማይበገር ነገዋን ለመገንባት ለምታደርገው ጥረት እንደገና ትነሳለች ብለዋል።
ነገ ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራችን አካል የሆነውን በአንድ ጀንበር 700 ሚሊየን ችግኞች የመትከል ዓላማን ለማሳካት እንነሳለን በማለት ገልጸዋል።
ከፍ ያለ ግብ ነው፤ ግን ጥንካሬያችንን፣ አንድነታችንን እና ለሕዝባችን ያለንን ቁርጠኝነት ያሳያል ሲሉም አስገንዝበዋል።
ይኽ ችግኝ ከመትከል በላይ ነው፤ ትንሽ ትልቅ፣ የከተማ የገጠር ሳንል ዜጎች ሁሉ አካባቢያችን እንዲያገግም፣ የውሃ ምንጮቻችን እንዲጠበቁ፣ የኑሮ ሁኔታችን እንዲሻሻል እንዲሁም ለመጪው ትውልዶች ዘላቂነት ያለው ነገን ለማረጋገጥ የምንሳተፍበት ተግባር ነው ብለዋል።
ሁላችሁም በዚህ ታላቅ ሥራ እንድትሳተፉ እና እንድታስተባብሩ አሳስባለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በጋራ ጠንካራ ዛፎችን ብቻ ሳይሆን ጠንካራ እና የበለጠ አረንጓዴ የሆነች ኢትዮጵያን እናሳድጋለንም ነው ያሉት።