ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ተስፋ ሰጪ ስራ እየተሰራ ነው – አበራ ዴሬሳ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብርና ተመራማሪ አበራ ዴሬሳ (ዶ/ር) መንግስት ምርታማነትን በማስፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየሰራ ያለው ስራ ተስፋ ሰጪ ነው አሉ፡፡
ከፋና ፖድካስት ጋር ቆይታ የነበራቸው አበራ ዴሬሳ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ ሰፊ የእርሻ መሬት፣ በቂ የውሃ ሃብት እንዲሁም አምራች የሰው ሃይል አላት ብለዋል።
እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች መንግስት በአግባቡ በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት።
ሀገሪቱ በርካታ የተፈጥሮ ጸጋን የተላበሰችና የተለያዩ ሰብሎችን ለማምረት የሚያስችል ሥነ ምህዳር ስላላት ገቢራዊ የሚሆኑ ፖሊሲዎችን በመቅረጽ ይበልጥ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል አንስተዋል፡፡
መንግስት ፖሊሲ በመቅረጽና ስራ ላይ በማዋል እንዲሁም ቆራጥ አመራር በመስጠት የሚያስመሰግን ተግባር ማከናወኑን ገልጸው፤ ስራውን በመከታተልና የስራው ባለቤት በመሆን ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል ስራ መስራት መቻሉን ጠቅሰው፤ መንግስት ባለፉት ዓመታት ለግርብርናው ዘርፍ በሰጠው ትኩረት በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል ነው ያሉት።
የስንዴ ምርታማነትን በማሳደግ ከውጪ ይገባ የነበረውን ማስቀረት መቻል፣ አቮካዶን ጨምሮ የተለያዩ ፍራፍሬዎችን ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንዲሁም የቡና ምርትን በማሳደግ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሉን በአብነት አንስተዋል።
የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማሳደግ በመንግስት በኩል የተሰራው ስራ ውጤታማ መሆኑን በማንሳት የገበያ እድልን በመፈጠር ሸማቹ በቀላሉ እንዲያገኝ ለማስቻል ይበልጥ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ምርቶቹን ወደ ግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ በማስገባት እሴት በመጨመር ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ካላት እምቅ አቅም አንጻር አሁንም በርካታ ስራዎች እንደሚቀሩ ገልጸው፤ የምርትን ጥራት እና መጠን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
መንግስት ለግብርና የሰጠው ትኩረት ትልቅ ውጤት ማምጣት ስለሚያስችል ሁሉም ባለድርሻዎች ተቀናጅተው ለዘርፉ ስኬት መረባረብ እንዳለባቸው አበራ ዴሬሳ (ዶ/ር) አመላክተዋል፡፡
በአቤል ንዋይ