ሴቶች የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አካል ካልሆኑ ሁለንተናዊ ለውጥ አይመጣም – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4 ፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሴቶች የኢኮኖሚ፣ማህበራዊና ፖለቲካዊ አካል ካልሆኑ ሁለንተናዊ ለውጥ አይመጣም አሉ በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፡፡
አቶ አደም የለውጡ ትሩፋት የሆኑ ሴት አመራሮች መድረክ ላይ እንዳሉት÷ ሴቶችን በሁሉም የልማት ዘርፍ ተሳታፊ ማድረግ ካልተቻለ ሁለንተናዊ ለውጥ ሊገኝ አይችልም፡፡
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው ÷ በዚህም አበረታች ውጤት ተገኝቷል ብለዋል፡፡
በተለይም ሴቶችን በሁለቱ ምክር ቤቶችና በተለያዩ ተቋማት ጭምር በሃላፊነት በመመደብ ውሳኔ ሰጪ እንዲሆኑ ጠንካራ ሥራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።
በኢኮኖሚው ዘርፍ በንቃት እንዲሳተፉና እንደ ሀገር የተያዙ ኢኒሼቲቮች እውን እንዲሆኑ አሻራቸውን በማሳረፍ ላይ ይገኛሉም ነው ያሉት።
በቀጣይም ሴቶችን በኢኮኖሚ ይበልጥ ማብቃት፣ የትምህርትና ክህሎት አቅማቸውን ማሳደግ እንዲሁም የአመራርና ውሳኔ ሰጪነት ሚናቸውን ማሳጠናከር ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
በታምራት ደለሊ